1እንደዚሁም፥ አብሮ እንደሚሰራ የእግዚአብሔርን ፀጋ እንዲሁ እንዳትቀበሉ እለምናችኋለሁ።
2ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሏልና "በምቹ ጊዜ ሰማሁህ በድነትም ቀን ረዳሁህ።" ልብ በሉ፥ ምቹ ጊዜም ሆነ የድነት ቀን አሁን ነው።
3አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በማንም ፊት ማሰናከያ አናኖርም።
4ከዚያ ይልቅ፥ በድርጊቶቻችን ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን እናረጋግጣለን። ይህም በመፅናት፥በመከራ፥ በስቃይ፥በችግር
5በመገረፍ፥ በእስራት፥ጥላቻ በተሞላ አመፅ፥ ፥በከባድ ስራ ፥እንቅልፍ በማጣት፥በርሃብ፥
6በንፅህና፥በእውቀት፥በትዕግስት፥በርህራሄ፥በመንፈስ ቅዱስ፥በእውነተኛ ፍቅር፥
7በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ሃይል ማለትም ለቀኝ እና ለግራ ለሚሆን ለፅድቅ የጦር ዕቃ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን።
8በክብርም ሆነ በውርደት፥ በሃሜትም ሆነ በሙገሳ ውስጥ እንሰራለን። በሃሰት ብንከሰስም እውነተኞች ሆነን ተገኝተናል።
9ያልታወቅን ሆነን ስንሰራ፥እንታወቃለን፤ የምንሞት ስንመስል ህያዋን ነን። በጥፋታችን እንደሚቅጣ ሰው ብንሆንም፥ሞት አልተፈረደብንም።
10እንደ ሃዘንተኞች ስንሰራ ሁልጊዜም ግን ደስተኞች ነን፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለፀጎች እናደርጋለን፥ ምንም የሌለን ስንሆን፥ ሁሉም አለን።
11የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ ሁሉን ነገር በግልፅ ነግረናችኋል፥ልባችንንም ለእናንተ ከፍተንላችኋል።
12ልባችሁ በራሳችሁ መሻት እንጂ በእኛ ምክንያት አልተዘጋም።
13ተገቢ በሆነ ሁኔታ እኔም እንደ ልጆች እናገራችኋለሁ፤ልባችሁን ክፈቱልን።
14ከማያምኑ ጋር በማይሆን መንገድ በአንድ ላይ አትተሳሰሩ። ፅድቅ ከአመፀኝነት ጋር ምን መዛመድ አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ህብረት አለው?
15ክርስቶስስ ከቤልዖር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምንስ ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?
16የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው? እግዚአብሔር "ከእነርሱም ጋር አድራለሁ፥በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸው እሆናለሁ፥ እነርሱም ህዝብ ይሆኑኛል" ብሎ ስለተናገረ እኛ የህያው እግዚአብሔር መቅደሶች ነን።
17ስለዚህም "ከመካከላቸው ውጡ፤የተለያችሁም ሁኑ" ይላል ጌታ፥ "እርኩሱን አትንኩ፥እኔም እቀበላችኋለሁ።
18አባት እሆናችኋለሁ እናንተም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ።" ብሏል ሁሉን የሚችል ጌታ።