1ስለዚህም በበኩሌ እንደገና ላስከፋችሁ ተመልሼ መምጣት አልፈለግሁም።
2ባስከፋችሁ እንኳ ሊያስደስተኝ የሚችለው ያው ያስከፋሁት ሰው አይደለምን?
3እንደፃፍኩላችሁ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባችው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ ነው። ስለሁላችሁም እርግጠኛ የምሆንበት በእኔ ያለ ደስታ በተመሳሳይ መልኩ በእናንተም ዘንድ ያለ መሆኑ ነው።
4የፃፍኩላችሁም በታላቅ ጭንቀት፥ በልብ መናወጥ እንዲሁም በብዙ እንባ ነበር፥ ምክንያቱ ደግሞ ለናንተ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳላሳዝናችሁ ነው።
5ማንም ያሳዘነ ሰው ቢኖር እኔን ብቻ ያሳዘነ ሳይሆን በተወሰነ መልኩ ሁላችሁንም ነው።
6ለዚያም ሰው በብዙዎች የደረሰበት ቅጣት ይበቃዋል።
7ግን ይህን ሰው በብዙ ሐዘን እንዳይዋጥ ከመቅጣት ይልቅ ይቅር ልትሉትና ልታፅናኑት ይገባል።
8ስለዚህም ለዚህ ሰው ፍቅራችሁን በይፋ እንድታረጋግጡለት አደፋፍራችኋለሁ።
9የፃፍኩላችሁ በሁሉ ነገር ታዛዦች መሆናችሁን እንድፈትንና እንዳውቅ ነው።
10አንድን ሰው ይቅር ብትሉት፣ እኔም ያንን ሰው ይቅር እለዋለሁ። እኔ ይቅር የምለው አንዳች ነገር ቢኖር ይቅርታ የማደርግለት በክርስቶስ ፊት ስለ እናንተ ስል ነው።
11ይህን የማደርገውም ሰይጣን እንዳያታልለን ነው። ምክንያቱም የርሱን እቅድ አንስተውምና።
12ምንም እንኳ ወደ ጥሮአዳ ስመጣ የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ በጌታ በር ተከፍቶልኝ ነበር። ሆኖም ወንድሜን ቲቶን በዚያ ስላላገኘሁት በአዕምሮዬ አላረፍኩም ነበር።
13ስለሆነም እነርሱን ትቼ ወደ መቄዶንያ ተመለስኩ።
14ነገር ግን ሁልጊዜ በክርስቶስ በድል ለሚመራን፥ ጣፋጭ የእውቀት ሽታ በየስፍራውም ለሚናኘው ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
15ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ ጣፋጭ ሽታ ነን።
16ለሚጠፉት ሰዎች፥ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ስንሆን ለሚድኑት ደግሞ ለህይወት የሚሆን የህይወት ሽታ ነን። ለነዚህ ነገሮች የበቃ ማነው?
17የእግዚአብሔርን ቃል ለትርፋቸው እንድሚነግዱበት እንደ ብዙዎች አይደለንም። በዚያ ፈንታ በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት፥ ከእግዚአብሔር እንደተላክን በቅን ልቦና እንናገራለን።