መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ቆሮንቶስ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ እና ወንድማችን ከሆነው ጢሞቲዎስ፥ በቆሮንቶስ ለምትገኝ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን እንዲሁም በመላው አካይያ ላሉ አማኞች ሁሉ፡
2ከእግዚአብሔር ከአባታችን እንዲሁም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋና ሰላም ለናንተ ይሁን።
3የምህረት አባት፥ የመፅናናት አምላክ እና በመከራችን ሁሉ የሚያፅናናን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።
4እግዚአብሔር በመከራችን ሁሉ ያፅናናል፥እኛም ራሳችን በእርሱ በእግዚአብሔር በተፅናናንበት መፅናናት ልክ ሌሎችን ማፅናናት እንችላለን።
5ምክንያቱም የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደበዛ፥ መፅናናታችንም በክርስቶስ በኩል እንዲሁ ይበዛልናል።
6ነገር ግን መከራን ብንቀበል፥ስለናንተ መፅናናት እና ድነት ነው። ወይንም ደግሞ የእኛ መፅናናት የእናንተም መፅናናት ማለት ነው፤ይህም እኛ በምንቀበለው መከራ እናንተም በተመሳሳይ መልኩ በትእግስት አብራችሁን ስለምትካፈሉ ነው።
7በናንተም ያለን መታመን ፅኑ ነው፥በመከራችን እንደምትካፈሉ ሁሉ በመፅናናታችንን ደግሞ እንደምትካፈሉ እናውቃለን።
8ወንድሞች ሆይ፥በእስያ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በህይወት ለመኖር ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ከብዶን ነበር።
9በርግጥም ሞት ተፈርዶብን ነበር። ሆኖም ግን ያ የደረሰብን መከራ ሙታንን በሚያስነሳ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን አደረገን።
10ከብርቱ ጥፋት አዳነን እንዲሁም ያድነናል። መታመናችንን በእርሱ ላይ አድርገናል፤እርሱም ይታደገናል።
11በእናንተም የፀሎት ድጋፍ አምላካችን ስራውን ይሰራል። በመቀጠልም በብዙዎች ፀሎት አማካኝነት ለእኛ ስለተሰጠው ሞገስ በርካቶች ምስጋናን ያቀርባሉ።
12የምንመካው በህሊናችን ምስክርነት ላይ ነው። ምክንያቱም በዚህ ዓለም ስንመላለስ የነበረው በንፁህ ህሊና እና ከእግዚአብሔር በሚሰጥ ቅንነት ነበር። በተለይም ከናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት የተመሰረተው በእግዚአብሔር ፀጋ ላይ እንጂ በምድራዊ ጥበብ ላይ አልነበረም።
13ልታነቡትና ልትረዱት የማትችሉትን አንዳችም ነገር አንዳልፃፍንላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤
14እናንተም በከፊል እንደተረዳችሁን በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ በእኛ እንደምትመኩ እኛም እንዲሁ በእናንተ እንመካለን።
15ስለዚህ ርግጠኛ ስለነበርሁ፥ በመጀመሪያ ወደናንተ መምጣት ፈለግሁ፤ ይህ ደግሞ በሁለቱም ጉብኝቶቼ ተጠቃሚዎች እንድትሆኑ ነው።
16ወደ መቄዶንያ ስሄድ ልጎበኛችሁ ፤ከዚያ ደግሞ ክመቄዶንያ ስመለስ ላያችሁ፤በኋላ ግን እናንተው ወደ ይሁዳ እንደምትልኩኝ አቅጄ ነበር።
17ይህንን ሳስብ ታዲያ የወላወልኩ ይመስላችኋልን? ወይስ በአንድ ጊዜ እንደ ሰው መስፈርት "አዎን፥ አዎን" እና "አይደለም፥አይደለም" በማለት አቀድኩን?
18ነገር ግን እግዚአብሔር የታመነ እንደሆነ፣ እኛም በሁለት ቃል "አዎን" እና "አይደለም" ብለን አንናገርም።
19ምክንያቱም በእናንተ መካከል በእኔ፥ በስልዋኖስ እና በጢሞቲዎስ የተሰበከው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በአንድ ጊዜ "አዎን" እና "አይደለም" አልነበረም፥ይልቅስ ሁልጊዜም በእርሱ "አዎን" ነው።
20በእርሱ የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሁሉ "አዎን" ናቸው። ስለዚህ እኛም በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር ክብር "አሜን" እንላለን።
21እንግዲህ እኛንም ከእናንተ ጋር በክርስቶስ የሚያፀናን እንዲሁም የሾመን እግዚአብሔር ነው።
22ለዚህም ወደፊት ለሚሰጠን ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን በልባችን የሰጠን ማህተሙንም ያደረገብን እርሱ ነው።
23ሆኖም ግን ወደ ቆሮንቶስ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ አስቤ እንደሆነ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።
24እኛም እምነታችሁ ምን መምሰል እንዳለበት በናንተ ላይ ልናዝዝ ሳይሆን በእምነታችሁ ፀንታችሁ እንድትቆሙ ለደስታችሁ የምንሰራ ነን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።