መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የሳባም ንግሥት የሰለሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በከባባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች፡፡ ቅመማ ቅመሞች፥ ብዙ ወርቆች እና በርካታ የከበሩ ማዕድናት ከተጫኑ ግመሎች ጋር ከብዙ ጓዝ ጋር መጣች፡፡ ወደ ሰለሞን በመጣች ጊዜ በልብዋ የነበረውን ሁሉ አጫወተችው፡፡
2ሰለሞንም ጥያቄዎችዋን ሁሉ መለሰላት፤ ለሰለሞንም የከበደው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ያልመለሰውም ምንም ጥያቄ አልነበረም፡፡
3የሳባም ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤተ መንግሥት፥
4በጠረጴዛው ላይ የነበረውን ምግብ፥ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥራ እና አለባበሳቸውን፥ አስተናጋጆቹንና አለባበሳቸውንም፥ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥም መስዋዕት የሚያቀርብበትን ሁኔታ ባየች ጊዜ አንዳች መንፈስ አልቀረላትም፡፡
5ንጉሡንም ፦ "ስለምትናገረው ነገርና ስለ ጥበብህ በገዛ አገሬ የሰማሁት ዘገባ እውነት ነው፤
6እዚህ እስክመጣ ድረስ ግን የሰማሁትን አላመንኩም ነበር፤ አሁን ዓይኖቼ አይተውታል፡፡ ስለ ጥበብህና ሃብትህ ግማሹ እንኳን አልተነገረኝም ነበር! ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ፡፡" አለችው፡፡
7"ጥበብህን ስለሚሰሙ ህዝብህ ምንኛ የተባረኩ፥ ዘወትር በፊትህ የሚቆሙ አገልጋዮችህም ምንኛ የተባረኩ ናቸው፡፡
8ለአምላክህ እግዚአብሔር ንጉሥ ትሆን ዘንድ ባንተ ደስ የተሰኘ እና በዙፋን ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ብሩክ ይሁን፡፡ አምላክህ እስራኤልን ለዘላለም ያፀናቸው ዘንድ ስለወደደ ፍትህንና ጽድቅን እንድታደርግላቸው በላያቸው ላይ አነገሠህ" አለችው፡፡
9ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ እና ከፍተኛ መጠን ያላቸው ቅመሞችንና የከበሩ ድንጋዮችን ሰጠችው፡፡ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰለሞን ከሰጠችው ከእደነዚህ የሚበልጥ መጠን ያላቸው ቅመሞች እንደገና ተሰጥቶት አያውቅም፡፡
10ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም አገልጋዮችና የሰለሞን አገልጋዮች የሰንደል እንጨትና የከበሩ ድንጋዮችን አመጡ፡፡
11ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለራሱ ቤት ደረጃዎችን እንዲሁም ለሙዚቀኞቹ በገናዎችንና መሰንቆዎችን/ክራሮችን አስደረገ፡፡ እንደዚህ ያለ እንጨት ከዚያ በፊት በይሁዳ ምድር ታይቶ አይታወቅም ነበር፡፡
12የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የበለጠ ንጉሥ ሰለሞን የተመኘችውን ሁሉ፥ የለመነችውንም ሁሉ ሰጣት፡፡ እርስዋም ተመልሳ ከአገልጋዮችዋ ጋር ወደ ራሷ ምድር ሄደች፡፡
13በአንድ ዓመት ለሰለሞን የመጣለት ወርቅ ክብደት ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበር፡፡
14ይህም ነጋድራሶችና ነጋዴዎች ካመጡት ወርቅ በተጨማሪ ነው፡፡ የዓረብም ነገሥታት ሁሉ እና የአገሪቱ ሹማምንት ለሰለሞን ወርቅና ብር ያመጡ ነበር፡፡
15ንጉሡም ሰለሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ ትልልቅ ጋሻዎችን ሠራ፡፡ በእያንዳንዳቸውም ውስጥ ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ ወርቅ ገብቶባቸው ነበር፡፡
16ከጥፍጥፍ ወርቅም ሦስት መቶ ጋሻዎችን ሠራ፡፡ በእያንዳንዱም ጋሻ ውስጥ ሦስት ምናን ወርቅ ገብቶበት ነበር፡፡ ንጉሡም በሊባኖስ ዱር ቤተ መንግሥት ውስጥ አስቀመጣቸው፡፡
17ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠርቶ ከሁሉ በበለጠ ወርቅ አስለበጠው፡፡
18ወደ ዙፋኑ የሚያደርሱ ስድስት ደረጃዎች ነበሩት፤ የዙፋኑም የላይኛው ክፍል ከጀርባው ክብ ነበር፡፡ በመቀመጫው በእያንዳንዱ ጎን በኩል የክንድ መደገፊያዎች እና ከመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፡፡
19በስድስቱም ደረጃዎች በእያንዳንዱ ላይ በእያንዳንዱ ጎን በኩል አንድ አንበሳ አስራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፡፡ በሌላ በየትኛውም መንግሥት እንደ እርሱ ያለ ዙፋን አልነበረም፡፡
20ንጉሥ ሰለሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ የወርቅ ነበሩ፤ በሊባኖስ ዱር ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከንፁህ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፡፡ በሰለሞን ዘመን ብር ዋጋ እንዳለው የማይቆጠር ስለነበር አንዳቸውም ብር አልነበሩም፡፡
21ከኪራም መርከቦች ጋር በመሆን በባሕር ላይ የሚሄዱ ብዙ መርከቦች ነበሩት፡፡ በየሦስት ዓመቱም አንድ ጊዜ መርከቦቹ ወርቅ፥ ብር እና የዝሆን ጥርስ እንዲሁም ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ይዘው ይመጡ ነበር፡፡
22በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን ከዓለም ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ፡፡
23ምድር ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰለሞንን መገኘት ይፈልጉ ነበር፡፡
24ከዓመት ዓመት የሚጎበኙትም ግብር፥ የብርና የወርቅ ዕቃዎች፥ አልባሳት፥ የጦር መሣሪያዎች እና ቅመማ ቅመሞች እንዲሁም ፈረሶችና በቅሎዎችን ያመጡ ነበር፡፡
25ሰለሞንም በሰረገሎች ከተሞችና ከራሱ ጋር በኢየሩሳሌም በተመደበላቸው ሥፍራ ለሚያኖራቸው ለፈረሶችና ለሰረገላዎች አራት ሺህ ጋጣዎች አስራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፡፡
26ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ይገዛ ነበር፡፡
27ንጉሡም በምድር ላይ እንዳለ ድንጋይ ያህል የበዛ ብር በኢየሩሳሌም ነበረው፡፡ የዝግባውንም እንጨት በቆላ እንዳሉት የሾላ ዛፎች የተትረፈረፈ እንዲሆን አደረገው፡፡
28ለሰለሞንም ከግብፅና ከየአገሩ ሁሉ ፈረሶችን ያመጡለት ነበር፡፡
29ሰለሞንን የሚመለከቱ ሌሎች ነገሮች የመጀመሪያውና የመጨረሻው በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራዕዩ በአዶ የተፃፉ አይደለምን?
30ሰለሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ፡፡
31ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፤ ሕዝቡም በአባቱ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ቦታ ነገሠ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።