1እስራኤልም ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም እየመጡ ስለነበር ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፡፡
2የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህንን ሰማ (ከንጉሡ ከሰለሞን ፊት ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ነበር፤ ነገር ግን ኢዮርብዓም ከግብፅ ተመለሰ)
3ልከውም አስጠሩት፤ ኢዮርብዓም እና እስራኤልም ሁሉ መጡ፤ ሮብዓምንም ተናገሩት፤
4"አባትህ ቀንበራችንን ከባድ አድርጎት ነበር፤ ስለዚህ አሁን አንተ ጽኑውን የአባትህን ሥራ ቀሊል፥ በእኛ ላይ ያደረገውንም ከባድ ቀንበር የማያስቸግር አድርግልን፤ እኛም እንገዛልሃለን" አሉት፡፡
5ሮብዓምም ፦ "ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ እኔ ተመልሳችሁ ኑ" አላቸው፤ ሕዝቡም ሄዱ፡፡
6ንጉሥ ሮብዓም፦ "ለእነዚህ ሰዎች መልስ እንድሰጣቸው እንዴት ትመክሩኛላችሁ?" ብሎ አባቱ ሰለሞን በሕይወት እያለ በፊቱ ይቆሙ የነበሩትን ሽማግሌዎች አማከራቸው፡፡
7እነርሱም ፦ "ለዚህ ሕዝብ መልካም ብታደርግላቸውና ብታስደስታቸው፥ በመልካም ቃል ብታናግራቸው ሁልጊዜ አገልጋዮችህ ይሆኑልሃል፤" ብለው ተናገሩት፡፡
8ሮብዓም ግን ሽማግሌዎቹ የመከሩትን ምክር ችላ ብሎ ከእርሱ ጋር ያደጉትን በፊቱም የሚቆሙትን ወጣቶች አማከራቸው፡፡
9"'አባትህ በእኛ ላይ ያደረገውን ቀንበር አቅልልልን' ላሉኝ ሰዎች መልስ እንድሰጣቸው ምን ምክር ትሰጡኛላችሁ?" አላቸው፡፡
10ከሮብዓም ጋር ያደጉት ወጣቶች ተናገሩት፦ "'አባትህ ሰለሞን ቀንበራችንን አከበደብን፤ አንተ ግን ልታቀልልን ይገባል' ብለው ለነገሩህ ሰዎች፦ 'ትንሿ ጣቴ ክአባቴ ወገብ ትወፍራለች' ልትላቸው ይገባል፡፡
11"በመሆኑም አሁን ምንም እንኳን አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ የነበረ ቢሆንም እኔ ቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ ነገር ግን እኔ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ" አላቸው፡፡
12በመሆኑም ንጉሡ፦ "በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመልሳችሁ ኑ" ባላቸው መሠረት ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ፡፡
13ንጉሡም በጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎችን ምክር ቸል አለ፡፡
14የወጣቶቹን ምክር ተከትሎ ተናገራቸው፤ "ቀንበራችሁን ይበልጥ አከብድባችኋለሁ፤ እጨምርባችኋለሁ፡፡ አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ ነገር ግን እኔ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ" አላቸው፡፡
15በመሆኑም ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም፤ እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአሒያ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብአም የተናገረውን ቃሉን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔር የተደረገ ክስተት ነበር፡፡
16እስራኤል ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ሲያዩ ሕዝቡ ፦ "ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይም ልጅ ምንም ርስት የለንም! እስራኤል ሆይ እያንዳንዳችሁ ወደየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፡፡ ዳዊት ሆይ የገዛ ራስህን ቤት ተመልከት" ብለው መለሱለት፡፡ በመሆኑም እስራኤል ሁሉ ወደየድንኳኖቻቸው ተመለሱ፡፡
17በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት በእስራኤል ሕዝብ ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው፡፡
18ከዚያም ንጉሡ ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡ ንጉሥ ሮብዓም ፈጥኖ በሰረገላው ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ፡፡
19በመሆኑም እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ አመጸ፡፡