1ሰለሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበትን ሃያው ዓመት መጠናቀቂያ ላይ
2ሰለሞን ኪራም የሰጠውን ከተሞች እንደገና ሠርቶ የእስራኤል ሰዎች እንዲኖሩባቸው አደረገ፡፡
3ሰለሞን ሐማትሱባን አጥቅቶ አሸነፋት፡፡
4በምድረ በዳም የነበረችውን ታድሞርን እና በሐማትም የሠራቸውን የዕቃ ቤቱን ከተሞች ሁሉ ሠራ፡፡
5በቅጥሮች፥ በበሮችና በመዝጊያዎች የተመሸጉትን የላይኛውን ቤትሆሮንን እና የታችኛዋን ቤትሆሮንን ከተሞች ሠራ፡፡
6የባዕላትንም ከተማ፥ ሰለሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላዎቹንም ከተሞች፥ የፈረሰኞቹንም ከተሞች እንዲሁም በኢየሩሳሌም፥ በሊባኖስ እና በግዛቱ ሥር በነበሩት ስፍራዎች ሊሠራ የተደሰተባቸውን ነገሮች ሁሉ ሠራ፡፡
7ከኬጢያውያን፥ ከአሞራውያን፥ ከፌርዜያውያን፥ ከኤዊያውያን እና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን የእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥
8የእስራኤል ሕዝብ ያላጠፉአቸውን በምድሪቱ ላይ ከእነርሱ በኋላ የቀሩትን ዝርያዎቻቸውን ሰለሞን እስከ ዛሬ ድረስ የግዳጅ የጉልበት ሠራተኞች አደረጋቸው፡፡
9ነገር ግን ሰለሞን የእስራኤል ሰዎችን አንድም የግዳጅ የጉልበት ሠራተኞች አላደረጋቸውም፤ ይልቁንም ወታደሮቹ፥ አዛዦቹ፥ ሹማምንቶቹ እና የሠረገሎቹና የፈረሰኞቹ አዛዦች አደረጋቸው፡፡
10እነዚህ ሁለት መቶ ሃምሳው፥ ሥራውን የሚሰሩትን ሰዎች የሚቆጣጠሩ የንጉሥ ሰለሞን ዋና ተቆጣጣሪዎችን የሚያስተዳድሩ ዋና ሹማምንቶችም ነበሩ፡፡
11ሰለሞንም፦ "የእግዚአብሔር ታቦት የደረሰበት ቦታ ሁሉ ቅዱስ ስለሚሆን ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት መኖር አይገባትም" በማለቱ ምክንያት የፈርኦንን ልጅ ከዳዊት ከተማ ውጪ ለእርሷ ወደ ሰራላት ቤት አመጣት፡፡
12ከዚያም ሰለሞን በመተላለፊያው ፊት ለፊት በሠራው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፡፡
13ዕለታዊው መርሀ ግብር በሚጠይቀው መሰረት መሥዋዕቶች አቀረበ፤ በሙሴ ትዕዛዝ የሚገኙትን መመሪያዎች በመከተል በሰንበታቱ ቀናት፥ በየመባቻዎቹ እና በተደነገጉት በዓላት በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓል፥ በየሰባቱ ሱባኤ በዓል እና በየዳሱም በዓል አቀረባቸው፡፡
14ሰለሞን የአባቱን የዳዊትን ትዕዛዝ በመከተል ካህናቱን በየክፍላቸው፥ ሌዋውያንንም ዕለታዊው መርሀ ግብር እንደሚጠብቅባቸው እግዚአብሔርን ለማወደስና በካህናቱ ፊት ለማገልገል በየሥራቸው መደባቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ይህንንም አዝዞ ስለነበር ደጅ ጠባቂዎችን ደግሞ በእያንዳንዱ በር በየክፍላቸው መደባቸው፡፡
15እነዚህ ሰዎች ንጉሡ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ማናቸውንም ጉዳይ ወይም መጋዘኖቹን በተመለከተ ከሰጠው ትዕዛዛቱ አላፈነገጡም፡፡
16እዚህ ላይ የእግዚአብሔር ቤት መሠረት ከተጣለበት ቀን አንስቶ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ የሰለሞን ሥራ ተከናወነ፡፡ በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቤት ተጠናቅቆ ጥቅም ላይ ዋለ ፡፡
17ከዚህ በኋላ ሰለሞን በኤዶምያስ ምድር የባሕር ዳርቻ ወዳሉት ወደ ዔጽዮንጋብር እና ኤላት ሄደ፡፡
18ኪራምም የባህርን ነገር በሚገነዘቡ መርከበኞች የሚታዘዙ መርከቦችን ላከለት፡፡እነርሱም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር ወደ ኦፊር ሄዱ፡፡ ከዚያም አራት መቶ ሃምሳ መክሊት ወርቅ ለንጉሥ ሰለሞን አመጡ፡፡