1ሰለሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መሥዋዕቶችን በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ፡፡
2የእርሱ ክብር ቤቱን ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም፡፡
3የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ እሳቱ ሲወርድና የእግዚአብሔር ክብር በቤቱ ላይ እንደነበር ያዩ ነበር፡፡ በድንጋዩ ወለል ንጣፍ ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና አቀረቡ፡፡ "መልካም ነውና የቃል ኪዳን ታማኝነቱም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና" አሉ፡፡
4ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፡፡
5ንጉሥ ሰለሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሃያ ሺህ በጎች በጎችና ፍየሎች ሰዋ፡፡ እንደዚህ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ፡፡
6ካህናቱም እያንዳንዳቸው በሚያገለግሉበት ቦታ ቆመው ሌዋውያኑም "የቃል ኪዳን ታማኝነቱ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና" በሚለው መዝሙር እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ንጉሥ ዳዊት ያዘጋጀውን የእግዚአብሔር የዜማ መሳሪያዎች ይዘው ቆመው ነበር፡፡ ካህናቱ ሁሉ በፊታቸው መለከቶቻቸውን ሲነፉ እስራኤላውያን ሁሉ ቆሙ፡፡
7ሰለሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት ለፊት የነበረውን የአደባባዩን መካከል ቀደሰ፡፡ በዚያም የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉን ቁርባንና ስቡን መያዝ ስላልቻለ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሕብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ አቀረበ፡፡
8በዚያን ጊዜ ሰለሞን ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከሐማት መግቢያ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ የመጡ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ለሰባት ቀናት ለሰባት ቀናት በዓል አደረጉ፡፡
9መሠዊያውን ለሰባት ቀናት ቀድሰው እና በዓሉን ለሰባት ቀናት ጠብቀው ስለነበር በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ፡፡
10ሰለሞንም በሰባተኛው ወር በሃያ ሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር ለዳዊት፥ ለሰለሞንና ለሕዝቡ ለእስራኤል ካሳየው በጎነት የተነሳ በደስታና በሐሴት ልብ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፡፡
11በመሆኑም ሰለሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የገዛ ራሱን ቤት ጨረሰ፡፡ ለእግዚአብሔር ቤትና ለገዛ ራሱ ቤት ሰለሞን በልቡ ያሰበውን ማናቸውንም ነገር በስኬት አከናወነ፡፡
12እግዚአብሔርም በሌሊት ለሰለሞን ተገልጦ፦" ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንንም ስፍራ ለራሴ የመስዋዕት ቤት እንዲሆን መርጫለሁ" አለው፡፡
13ዝናብ እንዳይኖር ሰማያትን ብዘጋ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣን ባዝዘው ወይም በሕዝቡ መካከል ቸነፈርን ብሰድድ
14በስሜ የተጠሩት ህዝቤ ራሳቸውን ቢያዋርዱ፥ ቢጸልዩ፥ ፊቴን ቢፈልጉና ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ ከሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ፡፡
15አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚደረግ ጸሎት ዓይኖቼ ክፍት ይሆናሉ፤ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ፡፡
16አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህንን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ፡፡
17አንተ ደግሞ ያዘዝሁህን ሁሉ በመፈጸም እና ሥርዓቶቼንና ሕግጋቴን በመጠበቅ አባትህ ዳዊት እንደሄደ በፊቴ ብትሄድ፥
18ከአባትህ ከዳዊት ጋር በገባሁት በቃል ኪዳን "ከዘርህ በእስራኤል ላይ አለቃ የሚሆን አይታጣም" እንዳልኩት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ፡፡
19ነገር ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱና በፊታችሁ ያኖርኳቸውን ሥርዓቶቼንና ትዕዛዛቶቼን ብትተዉ፥ ሄዳችሁ ሌሎችንም አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥
20ያን ጊዜ ከሰጠኋችሁ ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስኩትን ይህንን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፡፡ በሕዝቦችም ሁሉ መካከል ምሳሌና መቀለጃ አደርገዋለሁ፡፡
21ምንም እንኳን ይህ ቤተ መቅደስ እጅግ የላቀ ቢሆንም በአጠገቡ የሚያልፉ ሰዎች ይደነግጣሉ፤ በጥላቻ ይነጋገራሉ፡፡ "እግዚአብሔር በዚህ ምድርና በዚህ ቤት ላይ ይህንን እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው?" ብለው ይጠይቃሉ፡፡
22ሌሎችም፦ "ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክትን የሙጥኝ ከማለታቸው የተነሳ ፥ ስለሰገዱላቸው ስላመለኳቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ አደጋ ያመጣባቸው" ብለው ይመልሳሉ፡፡