1ሰለሞንም፦"እግዚአብሔር በድቅድቅ ጨለማ እንደሚኖር ተናግሯል፤
2እኔ ግን ለዘላለም እንድትኖርበት የላቀ መኖሪያ ቤት ሠራሁልህ" አለ፡፡
3ከዚያም የእስራኤል ጉባኤ ቆመው በነበሩበት ንጉሡ ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ ባረከ፡፡
4እርሱም ፦ "ለአባቴ ለዳዊት የተናገረ እና በገዛ እጆቹ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤
5"ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ የሚሆንበት ቤት በዚያ ይሠራልኝ ብዬ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥኩም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አንድም ሰው አልመረጥኩም፤
6ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲሆንባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ" ብሎአል፡፡
7አሁንም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት መስራት በአባቴ በዳዊት ልብ ነበር፡፡
8ነገር ግን እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፦ "ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ ነበረ፤ ያ በልብህ የነበረ መሆኑ መልካም አደረግህ፡፡
9ነገር ግን ቤቱን አንተ ልትገነባው አይገባም፤ ይልቁንም ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራልኛል" አለው፡፡
10እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፈንታ ስለተነሳሁ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ስለተቀመጥሁ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ፈጽሞአል፡፡ ለእስራኤል አምላክም ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ፡፡
11ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦቱን በዚያ ውስጥ አኖርሁ፡፡
12ሰለሞን የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ባሉበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ፡፡
13ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱ አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መድረክ ሰርቶ ነበር፡፡ በአደባባዩም መሃል ላይ አድርጎት ነበር፡፡ በእርሱም ላይ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፡፡
14እንዲህም አለ፦ "የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ከሚሄዱ ባሪያዎችህ ጋር ኪዳንንና የቃል ኪዳን ታማኝነትን የምትጠብቅ በሰማይም ሆነ በምድር እንዳንተ ያለ አምላክ የለም፤ ለባሪያህ
15ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ አንተ፥ አዎ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደሆነው በእጅህ ፈጽመኸዋል፡፡
16አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፦ "'አንተ በፊቴ እንደተመላለስህ ልጆችህ በሕጌ ይሄዱ ዘንድ ቢጠነቀቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም' በማለት የሰጠኸውን ተስፋ ፈጽምለት፡፡
17እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ሆይ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም፡፡
18በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ መላው አጽናፈ ዓለም እና ሰማየ ሰማያት ራሱ ሊይዝህ አይችልም - ይልቁንም እኔ የሠራሁት ቤት ምንኛ ያነሰ ይችላል!
19ነገር ግን እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ የባሪያህን ይህንን ጸሎትና ልመናውን እባክህን ተቀበል፤ ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጩኸትና ጸሎት ስማ፡፡
20ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ስምህን እንደምታደርበት ወደተናገርከው ወደዚህ ስፍራ ዓይኖችህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ በቀንና በሌሊት የተገለጡ ይሁኑ፡፡
21ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልዩበት ጊዜ ልመናዎቻቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ስፍራ ከሰማያት ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል፡፡
22አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት ውስጥ በመሠዊያህ ፊት ቢምል
23ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በደሉን በራሱ ላይ በማድረግ በደለኛውን መልሰህ በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፡፡ ለጽድቁ ብድራትን ለመስጠት ጻድቁ ንጹህ መሆኑንም አስታውቅለት፡፡
24ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ሲነሱ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ በዚህም ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ ስምህን ቢጠሩ፥ ቢጸልዩና ምህረትን ቢለምኑ
25እባክህን ከሰማያት ስማና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሳቸው፡፡
26አንተን ከመበደላቸው የተነሳ ሰማያት ቢዘጉና ምንም ዝናብ በማይኖርበት ጊዜ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህን ቢጠሩና ስታስጨንቃቸው ከኃጢአታቸው ቢመለሱ
27ከሰማይ ስማ፤ ሊመላለሱበት ወደሚገባቸው መልካሙ መንገድ ስትመራቸው የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፡፡ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ በሰጠሃት በምድርህ ላይ ዝናብን ላክ፡፡
28በምድሪቱ ላይ ርሃብ ቢኖር ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢኖር ወይም ጠላቶች በምድራቸው ውስጥ የከተማ በሮችን ቢያጠቁ ወይም ማናቸውም መቅሰፍት ወይም ደዌ ቢኖር
29አንድም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ እያንዳንዱ መቅሰፍቱንና ሐዘኑን በልቡ አውቆ ወደዚህ ቤተ መቅደስ እጆቹን ዘርግቶ ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ
30በሰማይ በምትኖርበት ሆነህ ስማ፤ ይቅርም በል፤ የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለሆንክ ልቡን ታውቃለህ፤ ለእያንዳንዱ እንደ መንገዱ ሁሉ ብድራትን ስጠው፡፡
31ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህ በመንገድህም ይሄዱ ዘንድ ይህንን አድርግ፡፡
32ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ ባእድ ሰው ደግሞ ከታላቁ ስምህ ፥ ከኃያሉ እጅህና ከተዘረጋችው ክንድህ የተነሳ ከሩቅ አገር ሲመጣ፥ ወደዚህ ቤተ መቅደስ መጥተው በሚጸልዩበት ጊዜ
33በሰማይ በምትኖርበት ስፍራ ሆነህ ስማ፤ በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ስምህን እንዲያውቁ፥ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል እንዲፈሩህ እና ይህ የሠራሁት ቤት በስምህ የሚጠራ መሆኑን እንዲያውቁ ባእዱ ሰው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ፡፡
34ሕዝብህ አንተ በምትልካቸው በምንም መንገድ ከጠላቶቻቸው ጋር ለመዋጋት ቢወጡ ፥ አንተ ወደመረጥካት ወደዚች ከተማና ለስምህ ወደሠራሁት ወደዚህ ቤት ቢጸልዩ
35ከሰማያት ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ስማና በጉዳያቸው አግዛቸው፡፡
36ኃጢአት የማይሰራ ማንም የለምና አንተን በበደሉህ ጊዜ ተቆጥተሃቸውም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው ጠላት ወደ ቅርብም ሆነ ሩቅ አገር ቢያግዛቸውና እንደ ምርኮኛ ወደ ምድራቸው ቢወስዳቸው
37በግዞት አገር ውስጥ መሆናቸውን ቢገነዘቡ፥ ንስሃ ቢገቡና በተማረኩበት ምድር ሞገስን ካንተ ቢፈልጉ፥ 'ጠማማን ነገር አድርገናል፤ በድለናል፤ እኩይ ምግባር ፈጽመናል፤' ቢሉ
38ምርኮኛ ተደርገው በተወሰዱባት በተማረኩባት ምድር በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው ወዳንተ ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደሰጠሃቸው ምድር፥ ወደ መረጥካት ከተማና ለስምህ ወደሠራሁት ቤት ቢጸልዩ
39በሰማያት በምትኖርበት ስፍራ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ስማና በጉዳያቸው አግዛቸው፡፡ የበደሉህን የሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በል፡፡
40አሁንም አምላኬ ሆይ በዚህ ስፍራ ወደሚደረገው ጸሎት ዓይኖችህ የተገለጡና ጆሮዎችህ የሚያተኩሩ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ፡፡
41አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ አንተና የኃይልህ ታቦት ወደ ማረፊያህ ስፍራ ተነስ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ካህናትህ ደህንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በመልካምነትህ ደስ ይበላቸው፡፡
42እግዚአብሔር አምላክ ሆይ የቀባኸውን ሰው ፊት ካንተ አትመልሰው፡፡ ለባሪያህም ለዳዊት ያደረግህለትን የቃል ኪዳን ታማኝነት አስብ፡፡