1ሰለሞንም እንደዚህ ለእግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተጠናቀቀ፡፡ ሰለሞንም አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን እቃዎች ብሩን፥ ወርቁንና የቤት እቃዎችን ሁሉ ጨምሮ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበሩት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጣቸው፡፡
2ከዚያም ሰለሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ማለትም ከጽዮን እንዲያመጡ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ፥ የነገድ አለቆችን ሁሉ እና የእስራኤልን ሕዝብ ቤተሰብ መሪዎች ሰበሰበ፡፡
3የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ወቅት በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ፡፡
4የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሱ፡፡
5ታቦቱንም፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ቅዱሳት ዕቃዎች በሙሉ አመጡ፡፡ ከሌዊ ነገድ የነበሩት ካህናት እነዚህን ነገሮች ሁሉ አመጡ፡፡
6ንጉሥ ሰለሞንና የእስራኤል ማህበር ሁሉ ሊቆጠሩ የማይችሉትን በጎችና በሬዎች እየሰዉ በታቦቱ ፊት ተሰበሰቡ፡፡
7ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ቦታው አመጡት፡፡
8ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሸከሚያዎቹን ምሶሶዎችም ይሸፍኑ ነበር፡፡
9መሸከሚያዎቹ ምሶሶዎችም እጅግ ረጅም ከመሆናቸው የተነሳ ጫፎቻቸው ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ከቅዱሱ ሥፍራ ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ክውጪ መታየት አይችሉም ነበር፡፡ እስከዚህች ቀንም ድረስ በዚያ ይገኛሉ፡፡
10በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ሰዎች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በስተቀር ምንም ነገር አልነበረባቸውም፡፡
11ካህናቱም ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ወጡ፡፡ በዚያ የነበሩትም ካህናት በተመደቡበት ክፍል ላይ ሳያተኩሩ ሁሉም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ቀድሰው ነበር፡፡
12መዘምራን የነበሩትም ሌዋውያንም አሳፍን፥ ኤማንን፥ ኤዶታምን ልጆቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ጨምሮ ሁሉም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽል፥ በገና እና መሰንቆ/ክራር እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በስተምሥራቅ ቆመው ነበር፡፡ ከእነርሱም ጋር መቶ ሃያ መለከት የሚነፉ ካህናት ነበሩ፡፡
13መለከቱን የሚነፉትና መዘምራኑም ከመቅደሱ ሲወጡ በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያወደሱ በአንድ ቃል ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር፡፡ ከመለከቶቹና ከጸናጽሎቹ ከሌሎቹም መሳሪያዎች ጋር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፡፡" ቸር ነውና የቃል ኪዳን ታማኝነቱ ለዘላለም የሚጸና ነውና" ብለው ዘመሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ቤቱ የእግዚአብሔር ቤት በደመና ተሞላ፡፡
14የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ሞልቶት ስለነበር ከደመናው የተነሳ ካህናቱ ለማገልገል መቆም አልቻሉም ነበር፡፡