1በተጨማሪም የናሱን መሠዊያ ሠራ፤ ርዝመቱ ሃያ ክንድ ነበር፤ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ቁመቱም አሥር ክንድ ነበር፡፡
2ክፈፉ ከጫፍ እስከ ጫፉ አሥር ክንድ የሆነ ከቀለጠ ብረት ትልቅ ክብ ውሃ መያዣ ኩሬም ሠራ፡፡ ቁመቱም አምስት ክንድ ነበር፤ ዙሪያውም ሰላሳ ክንድ ነበር፡፡
3ውሃ መያዣው ቀልጦ ሲሰራ ከአርሱ ጋር አብረው የተሠሩ ከውሃ መያዣው ዙሪያ ከክፈፉ በታች በእያንዳንዱ ክንድ ርቀት አሥር ኮርማዎች ነበሩበት፡፡
4ውሃ መያዣው ሦስቱ ወደ ሰሜን በሚመለከቱ፥ ሦስቱ ወደ ምዕራብ በሚመለከቱ፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ በሚመለከቱ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ በሚመለከቱ በአሥራ ሁለት በሬዎች ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ውሃ መያዣው በላያቸው ላይ ሆኖ የጀርባ የሠውነት ክፍላቸው በስተ ውስጥ ነበር፡፡
5ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበር፡፡ የአፉ ክፈፍም እንደ ጽዋ ከንፈር እንደ ፈነዳ የሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፡፡ ሦስት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ውሃ ይይዝ ነበር፡፡
6ደግሞም የተለያዩ ነገሮችን ማጠቢያ አሥር ጎድጓዳ ሳህኖች ሠራ፤ አምስቱን በስተግራ አምስቱንም በስተቀኝ አኖራቸው፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ለማቅረብ ጥቅም የሚሰጡ ነገሮች በውስጣቸው ይታጠቡባቸው ነበር፡፡ የውሃ መያዣው ኩሬ ግን ለካህናቱ መታጠቢያ ነበር፡፡
7ለንድፋቸው በተሰጠው መመሪያ መሠረት አሥሩን የወርቅ መቅረዞች ሠራ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተግራ አምስቱን በስተቀኝ አኖራቸው፡፡
8አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተግራ አምስቱን በስተቀኝ አኖራቸው፡፡ አንድ መቶ የወርቅ ጎድጓዳ ሳህኖች ሠራ፡፡
9በተጨማሪም የካህናቱን አደባባይ እና ታላቁንም አደባባይ የአደባባዮቹንም በሮች ሠራ፤ በሮቻቸውንም በናስ ለበጠ፡፡
10የውሃ መያዣውንም ኩሬ በቤቱ በስተቀኝ በስተምስራቅ ፊቱን ወደ ደቡብ አዙሮ አኖረው፡፡
11ኪራምም ምንቸቶቹን፥ መጫሪያዎቹንና መሠዊያውን መርጪያ ጎድጓዳ ሳህኖች ሠራ፡፡ ኪራምም እንደዚህ ለንጉሥ ሰለሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ -
12ሁለቱን አዕማድ፥ በሁለቱ አዕማድ ጫፍ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች፥ በሁለቱ አዕማድ ጫፍ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን ጌጠኛ ቅርፃ ቅርፆች ጨረሰ፡፡
13በአዕማዱ ጫፍ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ለሚሸፍኑት ሁለቱ ጌጠኛ ቅርፃ ቅርፆች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ተርታ ሮማኖች አድርጎ ለሁለቱ ጌጠኛ ቅርፃ ቅርፆች አራት መቶ ሮማኖች ሠራ፡፡
14ማቆሚያዎቹንና በማቆሚያዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰሃኖችንም ሠራ፤
15አንድ የውሃ መያዣ ኩሬ እና ከስሩ የሚሆኑትን አስራ ሁለት ኮርማዎች፥
16እንዲሁም ምንቸቶቹን፥ መጫሪያዎቹን፥ ሜንጦዎቹን እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ቁሳቁሶችን ሁሉ ሠራ፤ ኪራም ለንጉሥ ሰለሞን ለእግዚአብሔር ቤት ከአንፀባራቂ ናስ ሠራቸው፡፡
17ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና ዛሬታን መካከል በሸክላው መሬት ውስጥ ብረታ ብረቱ እንዲቀልጥ አስደረገ፡፡
18ሰለሞንም እነዚህን እቃዎች ሁሉ በብዛት እንዲሰሩ አስደረገ፤ በእርግጥም የናሱ ክብደት ሊታወቅ አይችልም ነበር፡፡
19ሰለሞን በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የቤት ዕቃዎች፥ የወርቁን መሠዊያ፥ የመገኘቱ ሕብስት የሚቀመጥባቸውን ገበታዎች፥
20በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ያበሩ ዘንድ የታቀዱትን መቅረዞችን ከቀንዲሎቹ ጋር ሠራ፡፡እነዚህ ከንጹሕ ወርቅ የተሰሩ ነበሩ፡፡
21አበባዎቹም፥ ቀንዲሎቹና መኮስተሪያዎቹም የጥሩ ወርቅ ነበሩ፡፡
22ጉጠቶቹም፥ ጎድጓዳ ሳህኖቹም፥ ማንኪያዎቹም ፥ እጣን ማጨሻዎቹም ሁሉ ከንጹህ ወርቅ የተሰሩ ነበሩ፡፡ ወደ ቤቱ ውስጥ መግቢያዎቹን በተመለከተ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚያስገቡት የውስጥ በሮች እና የቤቱ ማለትም የቤተ መቅደሱ በሮች ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፡፡