1ከዚህ በኋላ ሰለሞን እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠለት በሞሪያ ተራራ ላይ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ቤት መሥራት ጀመረ፡፡ ዳዊት እንዳቀደለት በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ሥፍራውን አዘጋጀ፡፡
2በነገሠ በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር በሁለተኛው ቀን መሥራት ጀመረ፡፡
3ሰለሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የጣለው መሠረት ስፍሮች እነዚህ ናቸው፡፡ ርዝመቱ በድሮው መለኪያ ስልሳ ክንድ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር፡፡
4በቤቱም ፊት የነበረው በረንዳ ርዝመቱ ከቤቱ ወርድ ተመሳሳይ ሆኖ ሃያ ክንድ ነበር፡፡ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበረ፡፡ ሰለሞንም ውስጡን በንጹህ ወርቅ ለበጠው፡፡
5የዋናውን ቤት ጣሪያ በጥድ እንጨት ሠራው፡፡ በንጹህ ወርቅም ለበጠው፡፡ የዘንባባ ዛፎችንና የሰንሰለቶችን አምሳል ቀረጸበት፡፡
6ቤቱንም በከበሩ ድንጋዮች አስጌጠው፤ ወርቁም የምሥራቅ ፈርዋይም ወርቅ ነበር፡፡
7አውታሮቹን፥ ሰረገሎቹን፥ ግድግዳዎቹንና በሮቹንም በወርቅ ለበጣቸው፡፡ በግድግዳዎቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረፀ፡፡
8ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም ከቤቱ ወርድ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሃያ ክንድ ነበር፤ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር፡፡ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅም ለበጠው፡፡
9የሚስማሮቹም ክብደት ሃምሳ ሰቅል ወርቅ ነበር፡፡ ከፍ ያሉ ገጽታዎቹን/ሰሌዳዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፡፡
10ለቅድስተ ቅዱሳን ሁለት የኪሩቤል አምሳያዎችን ሠራ፤ ባለሙያዎችም በወርቅ ለበጡዋቸው፡፡
11ክንፎቹ በአጠቃላይ ከዳር እስከ ዳር ሃያ ክንድ ይረዝሙ ነበር፡፡ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ ክፍሉ ግድግዳ ድረስ የሚደርስ አምስት ክንድ ይረዝም ነበር፤ ሌላኛው ክንፍ እንደዚሁ እስከ ሌላኛው ኪሩብ ክንፍ ድረስ የሚደርስ አምስት ክንድ ነበር፡፡
12የሌላኛው ኪሩብ ክንፍም ክፍሉ ግድግዳ ድረስ የሚደርስ አምስት ክንድ ይረዝም ነበር፤ ሌላኛው ክንፉም እንደዚሁ የመጀመሪያውን ኪሩብ ክንፍ የሚነካ አምስት ክንድ ነበር፡፡
13የእነዚህም ኪሩቤሎች ክንፎች በአጠቃላይ ሃያ ክንድ ያህል ተዘርግተው ነበር፡፡ ኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ዋናው ቤት እየተመለከቱ በእግሮቻቸው ቆመው ነበር፡፡
14ከሰማያዊም፥ ከሐምራዊም፥ ከቀዩም፥ ሐር እና ከጥሩ በፍታ መጋረጃውን ሠራ፤ የኪሩቤሎችንም ቅርፅ ሠራባቸው፡፡
15ሰለሞንም ለቤቱ ፊት ለፊት እያንዳንዳቸው ሠላሳ አምስት ክንድ ከፍታ ያላቸውን ሁለት ምሰሶዎች ሠራ፡፡ በእያንዳንዳቸውም ጫፍ ላይ የነበሩት ርዕሰ አእማድ አምስት ክንድ ከፍታ ያላቸው ነበሩ፡፡
16ለምሰሶዎቹም ሰንሰለቶችን አድርጎ በጫፋቸው ላይ አኖራቸው፡፡ መቶም ሮማኖች ሠርቶ ከሰንሰለቶቹ ጋር አገናኛቸው፡፡
17ምሰሶዎቹንም በቤት መቅደሱ ፊት ለፊት አንደኛውን በቀኝ ሌላኛውንም በግራ አቆማቸው፤ በስተቀኝ የነበረውን ምሰሶ የሚያቆም/ያኪን፥ የበስተግራውንም ምሰሶ የሚያበረታ/ቦኤዝ ብሎ ሰየመው፡፡