መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 35

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል አከበረ፤ በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካ ጠቦቶቹን አረዱ።
2ካህናቱን በየሥራ ቦታቸው አድርጎ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት አበረታታቸው።
3እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት ለእግዚአብሔር ለተሰጡት ሌዋውያን ፦ "ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰለሞን በገነባው ቤት ውስጥ አስቀምጡት። ከዚህ በኋላ በትከሻችሁ እየተሸከማችሁ አታዟዙሩት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ሕዝቡንም እስራኤልን አገልግሉ።
4በእስራኤል ንጉሥ ዳዊት የተጻፈና በልጁም በሰለሞን ጭምር የተሰጠውን መመሪያ በመከተል በየአባቶቻችሁ ቤቶችና በየሥራ ክፍላችሁ ስም ራሳችሁን አደራጁ።
5በሕዝቡ ዝርያዎች በወንድሞቻችሁ የአባቶች ቤቶች ውስጥ በየሥራ ክፍላችሁ የኃላፊነት ቦታችሁን በመያዝና በሌዋውያን አባቶች ቤቶች ውስጥ በየሥራ ክፍላችሁ ቦታችሁን በመያዝ በተቀደሰው ሥፍራ ቁሙ።
6የፋሲካውን ጠቦቶች እረዱ፤ እናንተም ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ። ለወንድሞቻችሁ ለእስራኤል ጠቦቶቹን ዝግጁ አድርጉላቸው፤ በሙሴ አማካይነት ለተሰጠው ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ አድርጉት።
7ኢዮስያስ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች ሰጠ። ሦስት ሺህ ወይፈኖችንም ሰጠ፤ እነዚህም የንጉሡ ኃብት ከነበሩት ነበሩ።
8መሪዎቹም ለህዝቡ፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የበጎ ፈቃድ ሥጦታዎችን ሰጡ። በእግዚአብሔር ቤት ባለሥልጣናት የነበሩት ኬልቅያስ፥ ዘካርያስና ይሒኤል ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ትንንሽ ከብቶችና ሦስት መቶ በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ።
9የሌዋውያኑ አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤልና ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት አምስት ሺህ ትንንሽ ከብቶችና አምስት መቶ በሬዎች ለሌዋውያኑ ሰጡ።
10በመሆኑም አገልግሎቱ ዝግጁ ነበረ፤ ካህናቱም ለንጉሡ ትዕዛዝ ምላሽ በመስጠት በየሥራ ክፍላቸው ከሆኑት ከሌዋውያኑ ጋር በየቦታቸው ቆመው ነበር።
11የፋሲካ ጠቦቶቹንም አረዱ፤ ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የጠቦቶቹን ቆዳቸውን ገፈፉ።
12በሙሴ መጽሐፍ እንደተጻፈ ለእግዚአብሔር ለማቅረብና በሕዝቡ የአባቶች ቤቶች መሠረት በየሥራ ክፍላቸው ሊያድሏቸው የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለይተው አስቀመጡ። በወይፈኖቹም ላይ እንደዚሁ አደረጉ።
13መመሪያዎቹን በመከተል የፋሲካውን ጠቦቶች በእሳት ጠበሷቸው። የተቀደሱትን ሥጦታዎች በምንቸቶች፥ በሰታቴዎችና በመጥበሻዎች ቀቀሏቸው፤ ለሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት አዳረሷቸው።
14ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱም መሥዋዕቱን አዘጋጁ፤ የአሮን ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን በማቅረብ እስከ ምሽት ድረስ በሥራ ተጠምደው ስለነበር ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ መሥዋዕቱን አዘጋጁ።
15ዳዊት፥ አሳፍ፥ ኤማንና የንጉሡ ባለ ራዕይ ኤዶታም በሰጡት መመሪያ መሠረት የአሳፍም ዝርያዎች መዘምራኑ በሥፍራቸው ቆመው ነበር። ጠባቂዎቹም በየበሮቹ ላይ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን መሥዋዕቱን ያዘጋጁላቸው ስለነበር የሥራ ቦታቸውን መልቀቅ አያስፈልጋቸውም ነበር።
16ስለዚህ ንጉሡ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብ፥ በዚያን ጊዜ መላው የእግዚአብሔር አገልግሎት የፋሲካን በዓል ለማክበር ተፈፀመ።
17በዚያን ቦታ ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ሕዝብ በዚያን ጊዜ ፋሲካውንና ከዚያም ለሰባት ቀናት የቂጣ በዓልን አከበሩ።
18ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ የፋሲካ በዓል በእስራኤል ተከብሮ አያውቅም፤ ከእስራኤልም ሌሎች ነገሥታት ሁሉ የትኛውም ኢዮስያስ ከካህናቱ፥ ከሌዋውያኑና ከይሁዳና እዚያ ከነበሩ ከእስራኤል ሕዝብና ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ጋር እንዳደረገው ያለ ፋሲካ አክብሮ አያውቅም።
19ይህ ፋሲካ የተከበረው ኢዮስያስ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ነበር።
20ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን ካስተካከለ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ ከርከሚሽን ሊዋጋ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊዋጋው ሄደ።
21ኒካዑ ግን ወደ እርሱ ፦" የይሁዳ ንጉሥ ሆይ ካንተ ጋር ምን አለኝ? ጦርነት የምዋጋው በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ ለጦርነት አልመጣሁብህም። እግዚአብሔር እንድፈጥን አዝዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር በሆነው በእግዚአብሔር ላይ ጣልቃ አትግባ፤ አለበለዚያ ያጠፋሃል" በማለት መልዕክተኞችን ላከበት።
22ነገር ግን ኢዮስያስ ከእርሱ መመለስን እምቢ አለ። ከእርሱ ጋር ለመዋጋት ራሱን በሌላ መልክ ሸፈነ። ከእግዚአብሔር አፍ የመጣውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፤ ስለሆነም በመጊዶ ሸለቆ ውስጥ ሊዋጋ ሄደ።
23ቀስተኞችም ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ለአገልጋዮቹ፦" ክፉኛ ቆስያለሁና ወደዚያ ውሰዱኝ" አላቸው።
24ስለዚህ አገልጋዮቹ ከሰረገላው አውርደው በሌላኛው ተጨማሪ ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት። ወደ ኢየሩሳሌምም ወሰዱት፤ በዚያም ሞተ። በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ። ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱለት።
25ኤርምያስም ለኢዮስያስ የሐዘን እንጉርጉሮ አወጣለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ውንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ ስለ ኢዮስያስ የሐዘን እንጉርጉሮ ያወጣሉ። እነዚህ መዝሙሮች በእስራኤል ልማድ ሆኑ፤ እነሆ በሐዘን እንጉርጉሮ መዝሙር ውስጥ ተጽፈዋል።
26ኢዮስያስን በተመለከተ ሌሎቹ ጉዳዮችና በእግዚአብሔር ሕግ ለተጻፈው ነገር በመታዘዝ ያደረጋቸው መልካም ድርጊቶች፥
27የእርሱ ድርጊቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።