መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 36

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የምድሪቱም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ቦታ በኢየሩሳሌም አነገሡት።
2ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ ሦስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ።
3የግብጽ ንጉሥ ከኢየሩሳሌም ከመንግሥቱ አስወገደው፤ ምድሩንም አንድ መቶ መክሊት ብርና አንድ መቶ መክሊት ወርቅ ቅጣት ጣለባት።
4የግብጽ ንጉሥ ወንድሙን ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ንጉሥ አደረገው፤ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። የኤልያቄምን ወንድሙን ኢዮአክስን ወሰደና ወደ ግብጽ አመጣው።
5ኢዮአቄም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉውን ነገር አደረገ።
6ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ጦርነት ከፍቶበት በሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው።
7ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃዎችም አንዳንዶቹን ወደ ባቢሎን ወሰደ፤ በባቢሎንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ አስቀመጣቸው።
8ኢዮአቄምን በተመለከተ ሌሎቹ ጉዳዮችና ያደረጋቸው አስጸያፊ ድርጊቶች፥ በእርሱ ላይ በክፉነት የተያዙበት ድርጊቶች እነሆ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። ልጁም ዮአኪን በእርሱ ቦታ ነገሠ።
9ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ ስምንት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወርና አሥር ቀን ነገሠ። በእግዚአብሔር ፊት ክፉውን ነገር አደረገ።
10በፀደይ ወራት ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰዎችን ልኮ ከእግዚአብሔር ቤት ከተወሰዱ የከበሩ ነገሮች ጋር ወደ ባቢሎን አመጣው፤ ዘመዱንም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።
11ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ አንድ ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ።
12በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ክፉውን ነገር አደረገ። ከእግዚአብሔርም አፍ በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊት ራሱን አላዋረደም።
13ሴዴቅያስም ታማኝ እንዲሆንለት በእግዚአብሔር እንዲምል ባደረገው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ አመፀ። ሴዴቅያስ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ላለመመለስ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ።
14በተጨማሪም የካህናቱ መሪዎችና ሕዝቡ የሌሎችን ሕዝቦች አስፀያፊ ነገሮች ምሳሌነት በመከተል እጅግ በጣም መተላለፍ አበዙ። እግዚአብሔር ለራሱ በኢየሩሳሌም የቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት በከሉት።
15የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ሥፍራ ከመራራቱ የተነሳ ደግሞ ደጋግሞ በመልዕክተኞቹ በኩል ቃል ይልክላቸው ነበር።
16እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሳ ድረስ፥ መሸሻ መንገድ እስከማይኖር ድረስ የእግዚአብሔርን መልዕክተኞች ይሳለቁባቸው፥ ቃሉንም ያቃልሉና በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።
17ስለዚህም እግዚአብሔር የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወጣቶቻቸውን በሰይፍ ገደላቸው፤ ለወጣቶቻቸው ወይም ለደናግልቱ፥ ለሽማግሌዎች ወይም ለሸበቶዎች አልራራም። እግዚአብሔር ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።
18የእግዚአብሔርንም ቤት እቃዎች ሁሉ ትልልቁንም ትንንሹንም የእግዚአብሔርንም ቤት ሃብትና የንጉሡንና የመሪዎቹን ሃብት እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ።
19የእግዚአብሔርን ቤት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምን አጥር አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን ሁሉ አቃጠሉ፤ በውስጧ ያሉትን ውብ ነገሮች ሁሉ አጠፉ።
20ከሰይፍም ያመለጡትን ንጉሡ ወደ ባቢሎን አጋዛቸው። የፋርስ መንግሥት አገዛዝ እስኪደርስ ድረስ ለእርሱና ለልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።
21ይህ የሆነው ምድሪቱ የሰንበት እረፍትዋን እስክታገኝ ድረስ በነቢዩ በኤርምያስ አፍ የተነገረውን የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈፀም ነው። በዚህ መንገድ ሰባ ዓመት በማሳለፍ ተትታ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ሰንበቷን አከበረች።
22በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈፀም በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ። እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ በጽሑፍም አደረገው።
23"የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የሚለው ይህ ነው፦ 'የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ለእርሱ ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል። በመካከላችሁ ከእርሱ ሕዝብ መካከል ማንም ቢሆን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ወደ ምድሪቱ ይውጣ" አለ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።