መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 33

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ምናሴ መንገሥ በጀመረ ጊዜ አሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሃምሳ አምስት ዓመት ነገሠ።
2እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዳስወጣቸው ሕዝቦች ዓይነት አስጸያፊ ነገር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች እንደገና ገነባ፤ ለበኣልም መሠዊያዎችን ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችንም አቆመ፤ ለሰማይም ከዋክብት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም።
4ምንም እንኳን እግዚአብሔር፦ "ስሜ ለዘላለም የሚኖረው በኢየሩሳሌም ነው" ብሎ ያዘዘ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ለጣዖታት መሠዊያዎችን ገነባ።
5በእግዚአብሔር ቤት ሁለቱ አደባባዮች ውስጥ ለሰማይ ከዋክብት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።
6በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት ውስጥ እንደሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ ሞራ ገላጭ ሆነ፤ አስማት አደረገ፤ መተተኛም ነበረ፤ ከሙታን ጋር ከሚነጋገሩና ከመናፍስት ጋር ከሚነጋገሩ ጋር ይማከር ነበር። በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፋት በመለማመድ እግዚአብሔርን ለቁጣ አነሳሳ።
7የአሼራን የተቀረጸ ምስል ሠርቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አኖረው፤ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን ሲናገር፦" ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ስሜ ለዘላለም እንዲኖርበት የመረጥኩት በዚህ ቤትና በኢየሩሳሌም ነው" ብሎ የነበረው ስለዚህ ቤት ነበር።
8በሙሴ አማካይነት የሰጠኋቸው ሕግ፥ ደንቦችና ድንጋጌዎች በመከተል ያዘዝኳቸውን ሁሉ ለመጠበቅ ቢጠነቀቁ ለአባቶቻቸው ከመደብኩላቸው ምድር የእስራኤልን ሕዝብ ከዚህ በኋላ አላወጣም" ብሎ ነበር።
9ምናሴም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ካጠፋቸው ሕዝቦች የበለጠ ክፋትን እንዲያደርጉ መራቸው።
10እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ነገር ግን አልሰሙትም።
11በመሆኑም የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በእግር ብረት ያዙት፤ በሰንሰለት አሰሩት፤ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት።
12ምናሴ በተጨነቀ ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ተማፀነ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።
13ወደ እርሱም ፀለየ፤ እግዚአብሔርም ተለመነው። እግዚአብሔር ልመናውን ሰምቶ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ንግሥናው መለሰው። ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ አወቀ።
14ከዚህ በኋላ ምናሴ በዳዊት ከተማ በግዮን ምዕራብ በኩል በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሣው በር መግቢያ ድረስ የውጫዊውን ግንብ ገነባ። የኦፊልንም ኮረብታ በእርሱ ከበበው። ግንቡንም እጅግ ታላቅ ከፍታ ድረስ አነሳው። በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ደፋር አዛዦችን አኖረ።
15የባዕድ አማልክትን ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አስወገደ፤ በእግዚአብሔር ቤት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም ውስጥ የገነባቸውን መሠዊያዎች ከከተማው ውጪ ወረወራቸው።
16የእግዚአብሔርም መሠዊያ አደሰ፤ የሕብረት መሥዋዕትና የምሥጋናን መሥዋዕት ሥጦታዎች አቀረበበት፤ የይሁዳ ሕዝብ የእስራኤልን አምላክ እንዲያገለግሉ አዘዘ።
17ነገር ግን ሕዝቡ እስከ አሁንም በኮረብታው መስገጃዎች ላይ ይሰዋ ነበር፤ ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።
18ምናሴን የሚመለከቱት ሌሎች ነገሮች ወደ አምላኩ የፀለየው ፀሎትና በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የተናገሩት የነቢያት ቃል እነሆ በእስራኤል ነገሥታት ድርጊቶች መካከል ተጽፈዋል።
19ፀሎቱም እግዚአብሔርም እንዴት እንደተለመነው፥ ኃጢአቱና መተላለፉ ሁሉ ራሱንም ከማዋረዱ በፊት የኮረብታ መስገጃዎች የገነባባቸው፥ የማምለኪያ አጸዶችንና የተቀረጹትን ምስሎች ያቆመባቸው ቦታዎች በባለ ራዕዮቹ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
20ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በገዛ ራሱ ቤት ውስጥ ቀበሩት። ልጁም አሞጽ በእርሱ ቦታ ነገሠ።
21አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ እድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ነገሠ።
22አባቱ ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። አሞጽ አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹ ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤ አመለካቸውም።
23አባቱ ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን አላዋረደም። ይልቁንም ይኸው አሞጽ መተላለፉን ይበልጥ ጨመረው።
24አገልጋዮቹ በእርሱ ላይ አሲረው በገዛ ቤቱ ውስጥ ገደሉት።
25የምድሪቱ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩበትን ሰዎች ሁሉ ገደሉ፤ ልጁንም ኢዮስያስን በእርሱ ቦታ አነገሡት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።