1ከእነዚህ ነገሮችና ከእነዚህ የታማኝነት ድርጊቶች በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፤ ለራሱ ሊይዛቸው ያሰባቸውን የተከበቡ ከተሞች ሊያጠቃ ሰፈረ።
2ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ ኢየሩሳሌምንም ሊዋጋ እንዳሰበ ባየ ጊዜ
3ከከተማው በስተውጪ የነበሩትን የምንጭ ውሃዎች ለመድፈን ከመሪዎቹና ከኃያላን ሰዎቹ ጋር ተመካከረ፤ እነርሱም እንደዚህ ለማድረግ ረዱት።
4በመሆኑም በርካታ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ምንጮቹን ሁሉና በምድሪቱ መካከል አልፎ ይፈስ የነበረውን ጅረት አስቆሙ። እነርሱም "የአሦር ነገሥታት መጥተው ለምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?" አሉ።
5ሕዝቅያስም ተደፋፈረና የፈረሰውን ቅጥር ሁሉ ጠገነ፤ እስከ ማማዎቹ ድረስ ሠራው፤ በስተውጪ ሌላ ግንብም ሠራ። በዳዊትም ከተማ ውስጥ የነበረችውን ሚሎንም አጠነከረ፤ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የጦር መሣርያዎችንና ጋሻዎችንም ሠራ።
6በሕዝቡ ላይም የጦር አዛዦችን አስቀመጠ። በአንድነትም በከተማይቱም በር በሰፊ ቦታ ወደራሱ ሰብስቦአቸው በማበረታታት ተናገራቸው።
7"በርቱ አይዞአችሁ። ከእርሱ ጋር ካሉት ከእኛ ጋር ያለው እርሱ እግዚአብሔር የሚበልጥ ስለሆነ ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ሠራዊት የተነሳ እንዳትፈሩ ወይም እንዳትደነግጡ።
8ከእርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ብቻ ነው፤ ከእኛ ጋር ግን ሊረዳንና ጦርነታችንን ሊዋጋልን ያለው አምላካችን እግዚአብሔር ነው" አላቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ራሳቸውን አጽናኑ።
9ከዚህ በኋላ የሦርያ ንጉሥ ሰናክሬም (በዚህ ጊዜ በለኪሶ ፊት ለፊት ነበረ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበሩ) አገልጋዮቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደነበሩት ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፤
10"የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የሚለው ይህንን ነው፦'በኢየሩሳሌም የተከበባችሁበትን ለመቋቋም የምትደገፉት በምን ላይ ነው?
11ሕዝቅያስ፦ 'አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ይታደገናል' ብሎ ሲነግራችሁ በረሃብና በጥማት እንድትሞቱ አሳልፎ ሊሰጣችሁ እያሳሳታችሁ አይደለምን?
12የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስወገደና 'በአንድ መሠዊያ ላይ ታመልካላችሁ፤ በእርሱም ላይ መሥዋዕታችሁን ታቃጥላላችሁ' ብሎ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ያዘዘው ይኸው ሕዝቅያስ አይደለምን?
13እኔና አባቶቼ በሌሎች ምድሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነው ምን እንደሆነ አላወቃችሁምን? የእነዚህ ምድሮች ሕዝቦች አማልክት በየትኛውም መንገድ ምድራቸውን ከኃይሌ ሊታደጉ ችለው ነበርን?
14አባቶቼ ሙሉ በሙሉ ካጠፏቸው ከእነዚያ ሕዝቦች አማልክት ሁሉ መካከል ሕዝቡን ከእጄ መታደግ የቻለ አምላክ ነበርን? አምላካችሁስ እናንተን ከኃይሌ ሊታደጋችሁ እንዴት ይችላል?
15አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ መንገድ አያታልልላችሁ ወይም አያሳምናችሁ። የየትኛውም ሕዝብ ወይም መንግሥት አማልክት ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ ሊታደግ ስላልቻለ አትመኑት። ይልቁንም አምላካችሁ ከእጄ እንዴት ሊያድናችሁ ይችላል?" አለ።
16የሰናክሬም አገልጋዮችም እግዚአብሔር አምላክና አገልጋዩ ሕዝቅያስ ላይ ይበልጥ የተቃውሞ ነገር ተናገሩ።
17ሰናክሬም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ላይ ለማፌዝና እርሱንም በመቃወም ለመናገር ደብዳቤዎችንም ጻፈ። "የምድሪቱ ሕዝቦች አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ እንዳልታደጉ እንደዚሁ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ አይታደግም" አለ።
18ከተማይቱን ለመያዝም በቅጥሩ ላይ የነበሩትን የኢየሩሳሌም ሰዎች ለማስፈራራትና ለማስጨነቅ በአይሁድ ቋንቋ በጎላ ድምጽ ይጮሁ ነበር።
19የሰዎች የእጅ ሥራ ብቻ በነበሩት በምድር ሌሎች ሕዝቦች አማልክት ላይ እንደተናገሩት በኢየሩሳሌም አምላክም ላይ ተናገሩ።
20ንጉሡ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ከዚህ ጉዳይ የተነሳ ፀለዩ፤ ወደ ሰማይም ጮኹ።
21እግዚአብሔርም መልአክን ላከ፤ እርሱም ተዋጊዎቹን ሰዎች፥ አዛዦቹንና የንጉሡን ባለሥልጣናት በሰፈሩበት ቦታ ገደላቸው። በመሆኑም ሰናክሬም አፍሮ ወደ ገዛ ምድሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩ ቤት በገባ ጊዜ እዚያ ከገዛ ራሱ ልጆች አንዳንዱ በሰይፍ ገደሉት።
22በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅና ከሌሎች ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በሁሉም መንገድም መራቸው።
23በርካቶችም ለእግዚአብሔር ሥጦታዎችን፥ የከበሩ ነገሮችንም ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡ ነበር። እርሱም ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሕዝቦች ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
24በዚያን ወቅት ሕዝቅያስ ለመሞት እስኪቀርብ ድረስ ታምሞ ነበር። ወደ እግዚአብሔርም ፀለየ፤ እርሱም ተናገረው፤ እንደሚፈወስም ምልክትን ሰጠው።
25ሕዝቅያስ ግን ልቡ ታብዮ ስለ ነበር እግዚአብሔር ለሰጠው እርዳታ ውለታ ቢስ ሆነ። በመሆኑም በእርሱ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ መጣባቸው።
26ቢሆንም ግን በኋላ ላይ ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት እርሱና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁለቱም ራሳቸውን አዋረዱ። የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።
27ሕዝቅያስ እጅግ ብዙ ባለጠግነትና ብዙ ክብር ነበረው። ለራሱም ለብር፥ ለወርቅ፥ ለከበሩ ድንጋዮችና ለቅመማ ቅመሞች እንዲሁም ለጋሻዎችና ዋጋ ላላቸው ነገሮች ሁሉ መጋዘኖችን ሠራ።
28ለእህል፥ ለአዲስ ወይንና ዘይት መጋዘኖች፥ ለሁሉም ዓይነት እንስሳት ጋጣዎችም ነበሩት። በጋጣቸውም መንጋዎችም ነበሩት።
29በተጨማሪም እግዚአብሔር እጅግ ብዙ ሃብት ስለሰጠው ለራሱ ከተሞችን፥ የተትረፈረፉ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ንብረት አዘጋጀ።
30የግዮንን የላይኛውን ውሃ ምንጮች የደፈነና በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል በቀጥታ ቁልቁል እንዲመጡ ያደረጋቸው ይኸው ሕዝቅያስ ነው። ሕዝቅያስም በሠራው ሥራ ሁሉ ተሳካለት።
31ነገር ግን በምድሪቱ ስለተደረገው ተዓምራዊ ምልክት የሚያውቁ ሰዎችን ጥያቄ ለመጠየቅ የተላኩትን የባቢሎን መሳፍንት መልዕክተኞችን በተመለከተ ጉዳይ እግዚአብሔር ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ለማወቅ ለራሱ ተወው።
32ሕዝቅያስን በተመለከተ ሌሎቹ ጉዳዮች የቃል ኪዳን ታማኝነት ድርጊቶቹን ጨምሮ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራዕይና በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ መጻፋቸውን መመልከት ትችላላችሁ።
33ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ዝርያዎች መቃብር በኮረብታው ላይ ቀበሩት። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በሞቱ ጊዜ አከበሩት። ልጁ ምናሴ በእርሱ ቦታ ነገሠ።