1ሁሉም ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ እዚያ የተገኙት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው የአምልኮ ድንጋይ ምሶሶዎችን ሰባበሩ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቹን ቆረጡ፤ በይሁዳና በብንያም ሁሉ መስገጃዎችንና መሠዊያዎችን ሰባበሩ፤ ሁሉንም እስኪያጠፉ ድረስ ይህንኑ በኤፍሬምና በምናሴም ጭምር አደረጉት። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ገዛ ምድሩና ወደ ገዛ ከተማው ተመለሰ።
2ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን በየሥራ ክፍል በማደራጀት ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ለእያንዳንዱ ሥራ በመስጠት በየአገልግሎታቸው መደባቸው። የሚቃጠል መሥዋዕትና የሕብረት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ እንዲያገለግሉ፥ እንዲያመሰግኑና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሮች እንዲያወድሱ መደባቸው።
3በእግዚአብሔር ሕግ ተጽፎ እንደነበረውም ለሚቃጠል መሥዋዕት ማለትም ለጠዋትና ለማታ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለሰንበት ቀናት፥ ለመባቻዎቹና ለመደበኛ በዓላትም የሚቃጠል መሥዋዕት ከንጉሡ ከገዛ ራሱ ሃብት ድርሻውን መደበ።
4በተጨማሪም ካህናቱና ሌዋውያኑ የእግዚአብሔርን ሕግ በመታዘዝ ላይ እንዲያተኩሩ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎች ለካህናቱና ሌዋውያኑ ድርሻቸውን እንዲሰጡ አዘዘ።
5ትእዛዙ እንደወጣም የእስራኤል ሕዝብ የእህሉን፥ የአዲሱን ወይን፥ የዘይቱን፥ የማሩን እንዲሁም ከእርሻው መከር ሁሉ በኩራት አትረፍርፈው ሰጡ፤ የሁሉንም ነገር አሥራትም አትረፍርፈው አመጡ።
6በይሁዳ ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ የበሬዎቹንና በጎቹን አሥራት፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የተሰጡ ነገሮችን ጭምር አሥራት አምጥተው ከምረው አስቀመጡት።
7በሦስተኛው ወር መከመር ጀምረው በሰባተኛው ወር ጨረሱ።
8ሕዝቅያስና መሪዎቹ መጥተው ክምሮቹን ሲያዩ እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ።
9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ።
10የሳዶቅም ቤት የሆነው ሊቀ ካህን ዓዛርያስ፦" ሕዝቡ ሥጦታዎቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣት ከጀመሩ አንስቶ በልተናል፤ ጠግበናልም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ስለባረከ ብዙ ተርፎአል። የተረፈውም ነገር ይህ እዚህ ያለው ታላቅ መጠን ነው" ብሎ መልስ ሰጠ።
11ከዚያም ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ መጋዘኖች እንዲዘጋጁ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጇቸው።
12ሥጦታዎቹን፥ አሥራቱንና የእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮች በታማኝነት አመጡ። ሌዋዊው ኮናንያ የበላያቸው አስተዳዳሪ ነበር፤ ወንድሙም ሰሜኢ በደረጃ ከእርሱ ቀጥሎ ሁለተኛ ነበረ። በንጉሡም በሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ላይ ባለ ሥልጣን በነበረው በዓዛርያስ የተሾሙ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች
13ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣኤል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ አስተዳዳሪዎች ነበሩ።
14ሌዋዊው የይምና ልጅ የምሥራቁ በር ጠባቂ ቆሬ ለእግዚአብሔር የተቀደሱትን ሥጦታዎችና በእግዚአብሔር የበጎ ፈቃድ ሥጦታዎች ላይ የበላይ ሆኖ ለእግዚአብሔር የቀረቡ ሥጦታዎችን ለማከፋፈል አዛዥ ነበር።
15ከበታቹም በካህናቱ ከተሞች ውስጥ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሽማያ፥ አማርያና ሴኬንያ ነበሩ። እነዚህን ሥጦታዎች ለታላላቆቹና ለታናናሾቹ ወንድሞቻቸው እንደየሥራ ክፍላቸው ለመስጠት በመታመን ሥልጣን ተሰጣቸው።
16በዕለታዊ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠበቅባቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገቡ ሁሉ በቦታቸው ሆነው በየሥራ ክፍላቸው ሥራቸውን ለመሥራት በዘር ሐረጋቸው ተቆጥረው የነበሩ ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ወንዶችም ሰጡ።
17በቦታቸው ሆነው በየሥራ ክፍላቸው ሥራቸውን ለመሥራት በአባቶቻቸው ቤቶች በዘር ሐረጋቸው ተቆጥረው የነበሩ ሌዋውያን ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑትም ሰጡ።
18በዘር ሐረጋቸው ተቆጥረው ለነበሩ ለሕፃናቱ፥ ለሚስቶቻቸው፥ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸው ሁሉ በመላው ሕዝብ መካከል በተቀደሰ ሁኔታ በአመኔታ ለተሰጣቸው ሥልጣን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ስለቀደሱ ለእነርሱም ሰጡ።
19በየከተማቸው ወይም በከተሞቹ ሁሉ ባሉ መንደሮች መስኮች ላይ ለነበሩ ለአሮን ዝርያዎች በካህናቱ መካከል ለሁሉም ወንዶች በስማቸው ድርሻቸውን ለመስጠትና በሌዋውያን መካከል እንደሆኑ በትውልድ ሐረጋቸው ለተቆጠሩ ሁሉ የተመደቡላቸው ሰዎች ነበሩ።
20ሕዝቅያስም ይህንን በይሁዳ ሁሉ አደረገ። በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት መልካም፥ ትክክለኛና ታማኝ ነገርን አከናወነ።
21በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት በጀመረው በየትኛውም ሥራ በሕጉና በትዕዛዛቱ አምላኩን ለመፈለግ በሙሉ ልቡ አከናወነው፤ እርሱም ተሳካለት።