መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 30

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ መልዕክተኞችን ላከ፤ ወደ ኤፍሬምና ምናሴም ደብዳቤዎችን ጻፈ።
2ንጉሡ፥ መሪዎቹና የኢየሩሳሌሙ ጉባዔ ሁሉ በአንድነት ከተመካከሩ በኋላ ፋሲካውን በሁለተኛው ወር ለማክበር እየወሰኑ ነበር።
3ካህናቱ በበቂ ቁጥር ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ስላልቀደሱና ሕዝቡም ገና ወደ ኢየሩሳሌም በአንድነት ስላልተሰበሰበ ወዲያውኑ በዓሉን ሊያከብሩ አልቻሉም ነበር።
4ይህ እቅድ በንጉሡና በጉባዔው ሁሉ ፊት መልካም ሆኖ ታይቶ ነበር።
5በመሆኑም በመላው እስራኤል ከቤርሳቤህ እስከ ዳን የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ለማክበር ሕዝቡ እንዲመጡ አዋጅ እንዲነገር ድንጋጌ አወጡ። በእርግጥም በጽሑፍ እንደታዘዘው በብዙ ቁጥር አላከበሩትም ነበር።
6በንጉሡ ትእዛዝ መልዕክተኞች ወደ መላው ይሁዳና እስራኤል ሁሉ የንጉሡንና የመሪዎቹን ደብዳቤ ይዘው ሄዱ። "እናንተ የእስራኤል ሰዎች ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠው ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃም፥ ይስሐቅና እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።
7እንደምታዩት ለጥፋት አሳልፎ እስኪሰጣቸው ድረስ በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ላይ እንደተላለፉት እንደ አባቶቻችሁ ወይም ወንድሞቻችሁ አትምሰሉ።
8አሁንም አባቶቻችሁ እንደነበሩት እናንተም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። ይልቁንም ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡና የጋለ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለማምለክ ለዘላለም ለእግዚአብሔር ወደ ተሰጠው ቅዱስ ሥፍራው ኑ!
9አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ስለሆነ ወደ እርሱ ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ ስለማይመልስ ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ እንደ እስረኛ በወሰዷቸው ሰዎች ፊት ሃዘኔታ ያገኛሉ። ወደዚህችም ምድር ይመለሳሉ።
10በመሆኑም መልዕክተኞቹ እስከ ዛብሎን ድረስ በመላው የኤፍሬምና የምናሴ ክልሎች ሁሉ ከከተማ ወደ ከተማ አለፉ፤ ሕዝቡ ግን ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም።
11ነገር ግን የተወሰኑ የአሴርና የምናሴ የዛብሎንም ሰዎች ራሳቸውን አዋርደው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
12በእግዚአብሔር ቃል የንጉሡንና የመሪዎቹን ትዕዛዝ ለመፈጸም አንድ ልብ ሊሰጣቸው የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይም መጣ።
13በሁለተኛው ወር የቂጣውን በዓል ለማክበር ብዙ ሰዎች፥ እጅግ ታላቅ ጉባዔ ለማክበር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
14ተነስተው በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ማጠኛዎች ሁሉ አስወገዱ፤ ወደ ቄድሮን ወንዝም ጣሉአቸው።
15ከዚያም በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን ጠቦቶቹን አረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ነበርና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።
16በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ የተሰጠውን መመሪያ በመከተል በየሥራ ክፍላቸው በቦታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር።
17በጉባዔው ውስጥ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያልሰጡ እጅግ ብዙ ነበሩ፤ ስለዚህ ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ጠቦቶቹን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ነጽተው ላልነበሩት ሰዎች ሁሉ የፋሲካውን ጠቦቶች የማረዱ ኃላፊነት የእነርሱ ነበር።
18እጅግ ብዙ ሰዎች ብዙዎቹም ከኤፍሬምና ከምናሴ፥ ከይሳኮርና ከዛብሎን በሕጉ መሠረት ራሳቸውን አላነጹም ነበር፤ ነገር ግን እንደ ተጻፈው ትዕዛዝ ባይሆንም የፋሲካውን ምግብ በሉ፤ ሕዝቅያስም ፦" ምንም እንኳን እንደ ቅዱሱ ሥፍራ የመንጻት መለኪያ መሠረት የነጻ ባይሆንም
19የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔር አምላክን ለመፈለግ በልቡ የቆረጠውን ሰው ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው" በማለት ፀልዮላቸው ነበር።
20እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።
21በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ሰዎች በታላቅ ደስታ የቂጣውን በዓል ለሰባት ቀናት አከበሩ። ሌዋውያኑና ካህናቱም ድምጹ በጎላ የሙዚቃ መሣሪያ ለእግዚአብሔር በመዘመር ከእለት ወደ እለት እግዚአብሔርን ያወድሱ ነበር።
22ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን አገልግሎት ያስተዋሉትን ሌዋውያን ሁሉ በማበረታታት ተናገራቸው። በመሆኑም የሕብረት ሥጦታ መሥዋዕት እያቀረቡና ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር እየተናዘዙ በሰባቱ ቀናት በዓል ሁሉ ይመገቡ ነበር።
23ከዚያም መላው ጉባዔ ለሌላ ሰባት ቀናት በዓሉን ለማክበር ወሰኑ፤ እንደዚህም በደስታ አደረጉ።
24የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለጉባዔው እንደ ሥጦታ ሰጥቶ ነበር፤ መሪዎቹም ለጉባዔው አንድ ሺህ ወይፈኖችና አሥር ሺህ በጎችና ፍየሎች ሰጡ። ብዙ ቁጥር ያላቸው ካህናትም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው ነበር።
25የይሁዳ ጉባዔ ሁሉ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር፥ ከእስራኤል በአንድነት የመጡት ሕዝብ ሁሉ፥ እንዲሁም ከእስራኤል ምድር እና በይሁዳ ይኖሩ ከነበሩት የመጡት እንግዶች ሁሉም ደስ አላቸው።
26በመሆኑም በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ነበር፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰለሞን ጊዜ አንስቶ እንደዚህ ያለ ነገር በኢየሩሳሌም ምንም አልነበረም።
27ከዚያም ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ ተነስተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምጻቸውም ተሰማ፤ ፀሎታቸውም ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ቅዱስ ሥፍራ ወደ ሰማይ አረገ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።