መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 29

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሕዝቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። የእናቱ ስም አቡ ነበር፤ የዘካርያስ ልጅ ነበረች።
2በማንኛውም ነገር የዝርያውን የዳዊትን ምሳሌ ተከትሎ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር አደረገ።
3በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ፤ አደሳቸውም።
4ካህናቱንና ሌዋውያኑን አምጥቶ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ላይ በአንድነት ሰበሰባቸው።
5"እናንተ ሌዋውያን ሆይ ስሙኝ! ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሱ፤ የአባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርንም ቤት ቀድሱ፤ ከተቀደሰው ሥፍራም ርኩሱን ነገር ሁሉ አስወግዱ" አላቸው።
6አባቶቻችን ሕጉን ስለተላለፉና በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ስላደረጉ፥ እርሱንም ትተውታል፤ ፊታቸውንም እግዚአብሔር ከሚኖርበት ሥፍራ መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም ሰጥተውታል።
7የበሮቹንም በረንዳዎች ዘግተዋል፤ መብራቶቹንም አጥፍተዋል። ለእስራኤል አምላክ በተቀደሰው ሥፍራ እጣን አላጠኑም ወይም የሚቃጠለውንም መስዋዕት አላቀረቡም።
8ስለዚህ የእግዚአብሔር ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ፤ በገዛ ራሳችሁ ዓይኖች ማየት እንደምትችሉት ለሽብር፥ ለድንጋጤና ለመዘበቻም ማረፊያ አደረጋቸው።
9ለዚህ ነው አባቶቻችን በሰይፍ የወደቁት፤ ለዚህም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ሚስቶቻችንም በምርኮ ውስጥ አሉ።
10አሁንም የጋለ ቁጣው ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ በልቤ አስቤአለሁ።
11ልጆቼ እግዚአብሔር በፊቱ ትቆሙ፥ ታመልኩትና፥ አገልጋዮቹ ልትሆኑና ዕጣንን ልታጥኑለት ስለመረጣችሁ አሁን ታካች አትሁኑ።
12ከዚያም ሌዋውያኑ የቀዓት ሰዎች የአሚሳ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ የሜራሪ ሰዎች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ የጌድሶን ሰዎች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፥
13የኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ የአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥
14የኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ የኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ።
15ወንድሞቻቸውን ሰብስበው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ቀደሱ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በመከተል ንጉሡ እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቤት ለማንጻት ወደ ውስጥ ገቡ።
16ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቤት ለማንጻት ወደ ውስጠኛው ክፍል ገቡ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትን ቆሻሻ ነገር ሁሉ ወደ ቤቱ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወደ ቄድሮን ዥረት ተሸክመው ሊወስዱት አወጡት።
17ቤቱን ለእግዚአብሔር መቀደስን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በወሩ በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር በረንዳ ደረሱ። የእግዚአብሔርን ቤት በስምንት ቀናት ቀደሱ። በመጀመሪያው ወር በአሥራ ስድስተኛው ቀን ጨረሱ።
18ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብተው፦" የእግዚአብሔርን ቤት፥ የሚቃጠል መስዋዕት የሚቀርብበትን መሠውያ ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር እና የመገኘቱን ሕብስት ገበታ ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር አንጽተናል።
19በተጨማሪም ንጉሥ አካዝ ነግሦ በነበረበት ጊዜ በመተላለፍ የወረወራቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ለእግዚአብሔር ቀድሰናል። እነሆ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ለፊት ይገኛሉ" አሉት።
20ከዚያም ንጉሡ ሕዝቅያስ በማለዳ ተነስቶ የከተማዋን መሪዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ።
21ለመንግሥቱ፥ ለቤተ መቅደሱና ለይሁዳ የኃጢአት መስዋዕት አድርገው ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባት አውራ በጎችና ሰባት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ወንድ ፍየሎች አመጡ። ካህናቱን የአሮንን ልጆች በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቧቸው አዘዛቸው።
22በመሆኑም ወይፈኖቹን አረዷቸውና ካህናቱ ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት። አውራ በጎቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ የበግ ጠቦቶቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት።
23ለኃጢአት መስዋዕት ወንድ ፍየሎቹን በንጉሡና በጉባዔው ፊት አመጧቸው፤ እጃቸውንም ጫኑባቸው።
24ካህናቱም አረዷቸው፤ ንጉሡም ለእስራኤል ሁሉ የሚቃጠል መስዋዕትና የኃጢአት መስዋዕት ሊደረግ እንደሚገባው አዝዞ ስለነበር ለእስራኤል ሁሉ ለማስተሰረይ በመሠዊያው ላይ ደማቸውን የኃጢአት መስዋዕት አደረጉት።
25ሕዝቅያስ ትዕዛዙ በነቢያቱ አማካይነት ከእግዚአብሔር ስለ ነበር በዳዊትና በንጉሡ ባለ ራዕይ በጋድ፥ በነቢዩ ናታንም ትዕዛዝ ሌዋውያኑን ከጽናጽል፥ ከበገናና ከመሰንቆ ጋር በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አደራጅቶ አስቀመጣቸው።
26ሌዋውያኑም ከዳዊት የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋርና ካህናቱ ከመለከቶች ጋር ቆሙ።
27ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲያቀርቡ አዘዛቸው። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ ሲጀመር የእግዚአብሔር መዝሙርም በመለከቶችና በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጀመረ።
28ጉባዔውም ሁሉ አመለኩ፤ መዘምራኑም ዘመሩ፤ መለከቶቹም ተነፉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ቀጠለ።
29መስዋዕት ማቅረቡን በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ አጎነበሱ፤ ሰገዱም።
30በተጨማሪም ንጉሡ ሕዝቅያስና መሪዎቹ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለራዕዩ በአሳፍ ቃል ለእግዚአብሔር ውዳሴ እንዲዘምሩ አዘዙ። በደስታም ውዳሴዎችን ዘመሩ፤ አጎነበሱ፤ ሰገዱም።
31ከዚያም ሕዝቅያስ፦"አሁን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል። ወደዚህ መጥታችሁ ለእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕቱንና የምስጋና መሥዋዕቱን አቅርቡ" አላቸው። ጉባዔውም መሥዋዕቱንና የምስጋና መሥዋዕቱን አቀረቡ፤ ፈቃደኛ ልብ የነበራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
32ጉባዔው ያቀረቡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቁጥር ሰባ ወይፈን፥ አንድ መቶ አውራ በጎችና ሁለት መቶ ወንድ ጠቦቶች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበሩ።
33ለእግዚአብሔር የተቀደሱት እንስሳት ስድስት መቶ በሬዎችና ሦስት ሺህ በጎች ነበሩ።
34ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠሉትን መሥዋዕት ሁሉ ለመግፈፍ እጅግ ጥቂት ነበሩ፤ በመሆኑም ወንድሞቻቸው ሌዋውያኑ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ፥ ሌዋውያኑም ከካህናቱ ይልቅ ራሳቸውን ለመቀደስ ይበልጥ ጥንቁቅ ስለ ነበሩ ካህናቱ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እስኪቀድሱ ድረስ ረዷቸው።
35በተጨማሪም እጅግ ብዙ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ነበሩ፤ ከሕብረት መሥዋዕት ስብ ጋር ይከናወኑም ነበር፤ ለእያንዳንዱም የሚቃጠል መሥዋዕት የመጠጥ መሥዋዕትም ነበር። በመሆኑም የእግዚአብሔር አገልግሎት በደንብ ተደራጅቶ ነበር።
36እግዚአብሔር ለሕዝቡ ካዘጋጀው ነገር የተነሳ ሥራው በፍጥነት በመከናወኑ ሕዝቅያስ ሕዝቡም ሁሉ ደስ አላቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።