1በዚህ ጊዜ ሰለሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤት እንዲገነባ እና ለመንግሥቱ ቤተ መንግሥት እንዲገነባ አዘዘ፡፡
2ጭነት የሚሸከሙ ሰባ ሺህ ሰዎች እና ከተራሮች እንጨት የሚቆርጡትን ሰማንያ ሺህ ሰዎች እነርሱንም የሚቆጣጠሩ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች መደበ፡፡
3ሰለሞንም ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ፦የሚኖርበትን ቤት እንዲሠራ የዝግባ እንጨት በመላክ ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ ለእኔም እንደዚሁ አድርግልኝ፡፡
4እነሆ በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ቅመም ሽታ ለማጠን፥ የመገኘቱን ኅብስት ዘወትር ለማኖር፥ በጠዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም ፥ በመባቻዎቹና ለአምላካችን ለእግዚአብሔር በተመደቡት ልዩ በዓላት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ልገነባና ልቀድሰው ነው፡፡ ይህ ለእስራኤል ለሁልጊዜ ሕግ ነው፡፡
5አምላካችን ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ስለሆነ የምሠራው ቤት እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡
6ነገር ግን መላው አጽናፈ ዓለምና ሰማይ ራሱ ሳይቀር ሊይዘው ለማይችለው ለእርሱ ለእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ የሚችል ማን ነው? በፊቱ መሥዋዕት ከማቅረብ በስተቀር ለእርሱ ቤት እሰራ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
7በመሆኑም በወርቅ፥ በብር፥ በናስ፥ በብረት፥ እንዲሁም ሐምራዊውን፥ ቀዩን፥ ሰማያዊውን ግምጃ በመሥራት የተካነ ሰው፥ የእንጨት ቅርጻ ቅርጽ ዓይነቶችን ሁሉ መሥራት የሚያውቅ ሰው ላክልኝ፡፡ እርሱም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት የተካኑ ሰዎች ጋር ይሆናል፡፡
8አገልጋዮችህ እንጨት ከሊባኖስ መቁረጥ እንደሚያውቁ ስለማውቅ ከሊባኖስ የዝግባ እንጨቶች፥ የጥድ እንጨቶች፥ የሰንደልም እንጨቶች ላክልኝ፡፡ እነሆ ባሪያዎችህ ከባሪያዎቼ ጋር ይሆናሉ፡፡
9ልሠራ ያሰብኩት ቤት ታላቅና ድንቅ ይሆናልና የተትረፈረፈ ሳንቃ እንጨት እንዲያዘጋጁልኝ ነው፡፡
10እነሆ እንጨቱን ለሚቆርጡ ሰዎች ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተፈጨ ስንዴ፥ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ለባሪያዎችህ እሰጣለሁ፡፡
11ንጉሥ ኪራም፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወዳቸው በላያቸው አንግሦሃል ብሎ መልሶ ወደ ሰለሞን መልእክት ላከ፡፡
12በተጨማሪም ኪራም፦ ሰማይንን ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔር ቤት እና ለመንግሥቱ ቤት የሚሠራ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለ፡፡
13አሁንም ማስተዋል የተሰጠውን የተካነውን ባለሙያዬን ሁራምን ልኬልሃለሁ፡፡
14ከዳን ሴት ልጆች የአንዲቱ ልጅ ነው፡፡ አባቱ የጢሮስ ሰው ነበር፡፡ ወርቁን፥ ብሩን፥ ናሱን፥ ብረቱን፥ ድንጋዩን እንዲሁም እንጨቱን፥ ሐምራዊውን፥ ሰማያዊንና ቀዩን ግምጃ ጥሩ በፍታውንም በመሥራት የተካነ ነው፡፡ የትኛውንም ዓይነት ቅርጽ በመሥራት እና የትኛውንም ዓይነት ንድፍ በማውጣትም የተካነ ነው፡፡ በተካኑት ሠራተኞችህ መካከል እና ከጌታዬ ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ስፍራ ይዘጋጅለት፡፡
15አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን እነዚህን ነገሮች ወደ አገልጋዮቹ ይላክ፡፡
16እኛም የሚያስፈልግህን ያህል እንጨት ከሊባኖስ እንጨት እንቆርጣለን፡፡ እንደ ታንኳ በባሕር ላይ ወደ ኢዮጴ እንወስድልሃለን፤ አንተም እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ታጓጉዘዋለህ፡፡
17ሰለሞንም ኣባቱ ዳዊት በእስራኤል ምድር የነበሩትን የውጪ አገር ዜጎች ሁሉ እንደቆጠረ እርሱ ያደረገበትን ዘዴ ተከትሎ ቆጠራቸው፡፡ እነርሱም አንድ መቶ ሃምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሆነው ተገኙ፡፡
18ሰባ ሺህው ጭነት እንዲሸከሙ ሰማንያ ሺህው በተራሮችም ላይ እንጨት እንዲቆርጡ እና ሦስት ሺህ ስድስት መቶው ደግሞ ሕዝቡን ለሥራ የሚያሰማሩ ተቆጣጣሪዎች እንዲሆኑ መደባቸው፡፡