1አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ ዓመቱ ነበረ፤ በኢየሩሳሌም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። ዝርያው ዳዊት እንዳደረገው በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር አላደረገም።
2ይልቁንም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ለበኣሊምም ከብረት ቀልጠው የተሠሩ ምስሎችን ሠራ።
3በተጨማሪም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዕጣን ዐጠነ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያሳደዳቸውን ሕዝቦች ክፉ ልማድ ተከትሎ ልጆቹን እንደሚቃጠል መሥዋዕት በእሳት ውስጥ አሳለፋቸው።
4በኮረብታው መስገጃዎች፥ በኮረብቶች ላይ እና በለመለመው ዛፍ ሁሉ በታች መስዋዕት ይሰዋና ዕጣን ያጥን ነበር።
5ስለዚህ የአካዝ አምላክ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው። ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ የብዙ እስረኞችን ስብስብ ከእርሱ ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡአቸው። አካዝ ለእስራኤልም ንጉሥ እጅ ተላልፎ ተሰጥቶ ነበር፤ እርሱም በታላቅ ግድያ አሸነፈው።
6የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመተዋቸው የተነሳ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ ሁሉም ደፋር የሆኑ አንድ መቶ ሃያ ሺህ ወታደሮችን ገደለ።
7ኤፍሬማዊው ኃይለኛ ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤተ መንግሥቱን ባለሥልጣን ዓዝሪቃምን ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ የነበረውን ሕልቃናን ገደለ።
8የእስራኤል ሠራዊት ከዘመዶቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሚስቶች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ምርኮ አድርገው ወሰዱ። ወደ ሰማሪያም ተሸክመው ያመጡትን እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
9ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ነበረ፤ ስሙም ዖዴድ ነበር። ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ሠራዊት ለመገናኘት ወጣ።" የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ስለተቆጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው። እናንተ ግን ወደ ሰማይ በሚደርስ ቁጣ ገደላችኋቸው።
10አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች እንደ ባሪያዎቻችሁ አድርጋችሁ ልትይዟቸው ታስባላችሁ። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ በገዛ ራሳችሁ ኃጢአት በደለኞች አይደላችሁምን?
11እንግዲያውስ አሁን ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር የጋለ ቁጣ በእናንተ ላይ ስለሆነ ከገዛ ወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን እስረኞች መልሳችሁ ስደዱ" አላቸው።
12ከዚያም የተወሰኑ የኤፍሬም ሰዎች መሪዎች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የስሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ ተመልሰው የመጡትን ተቃወሙአቸው።
13"መተላለፋችን ታላቅ ስለሆነና በእስራኤል ላይ የጋለ ቁጣ ስላለባት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት የሚሆንብንን ነገር ልታመጡብን፥ ኃጢአታችንንና መተላለፋችንን ልትጨምሩብን ስላሰባቸሁ እስረኞቹን እዚህ ልታመጧቸው አይገባችሁም" አሏቸው።
14የታጠቁት ሰዎችም እስረኞቹንንና ምርኮውን በመሪዎቹና በጉባኤው ሁሉ ፊት ተዉአቸው።
15በስማቸው የተመደቡትም ሰዎች ተነስተው እስረኞቹን ወስደው ከመካከላቸው እርቃናቸውን የነበሩትን ሁሉ ከተማረከው ልብስ አለበሷቸው። አጎናጸፉአቸው፤ ጫማም አደረጉላቸው። የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን ሰጡአቸው። ቁስላቸውን አከሙላቸው፤ የደከሙትንም በአህዮች ላይ አስቀመጧቸው። የዘንባባ ከተማ ተብላ በምትጠራዋ ኢያሪኮ ወዳሉት ቤተሰቦቻቸው መልሰው ወሰዷቸው። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16በዚያን ጊዜ ንጉሥ አካዝ እንዲረዱት እንዲጠይቋቸው ወደ አሦርያ ነገሥታት መልዕክተኞችን ላከ።
17የኤዶምያስ ሰዎች አንድ ጊዜ ደግመው መጥተው ይሁዳን በማጥቃት እስረኞችን ይዘው ወስደው ነበር።
18ፍልስጤማውያንም የቆላውን ከተሞች እና የይሁዳን ደቡባዊ ክልሎች ወርረው ነበር። ቤት ሳሚስንና ኤሎንን ፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮን ከነመንደርዎቿ፥ ተምናን ከነመንደርዎቿ እና ጊምዞን ከነመንደርዎቿ ወስደው ነበር። በእነዚያ ቦታዎችም ውስጥ ለመኖር ሄደው ነበር።
19በይሁዳ ክፉ ስላደረገና እግዚአብሔርንም እጅግ በጣም ስለበደለ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝ የተነሳ እግዚአብሔር ይሁዳን ዝቅ ዝቅ አድርጎ ነበር።
20የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልፌልሶር አካዝን በማበርታት ፈንታ መጥቶ አስጨንቆት ነበር።
21ለሦርያ ነገሥታት የከበሩትን ነገሮች ለመስጠት አካዝ የእግዚአብሔርን ቤት እና የንጉሡንና የመሪዎቹን ቤቶች ዘርፎ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አልጠቀመውም።
22ይኸው ንጉሥ አካዝ በመከራው ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ይበልጥ ኃጢአት ሠራ።
23ድል ላደረጉት አማልክት ለደማስቆ አማልክት መስዋዕት አቀረበ። "የሦርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለረዷቸው መስዋዕት ባቀርብላቸው እኔንም ይረዱኝ ይሆናል" አለ። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ ውድመት ሆኑ።
24አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት እቃዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሰብስቦ ሰባበራቸው። የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ዘጋ፤ ለራሱም በኢየሩሳሌም በየማዕዘኑ ሁሉ መሰዊያዎችን ሠራ።
25በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚቃጠልባቸው መስገጃዎችን ሠራ፤ በዚህ መንገድ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቁጣ ቀሰቀሰ።
26የአካዝ የተቀሩት ድርጊቶቹና መንገዶቹ ሁሉ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እነሆ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
27አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በከተማይቱ በኢየሩሳሌምም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላስገቡትም። ልጁ ሕዝቅያስ በእርሱ ቦታ ነገሠ።