መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 26

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ አሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ቦታ አነገሡት፡፡
2ኤላትን እንደገና የገነባትና ወደ ይሁዳ ወደቀድሞ ይዞታዋ የመለሳት እርሱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፡፡
3ዖዝያን መንገሥ በጀመረ ጊዜ አሥራ ስድስት ዓመቱ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌምም ሃምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፡፡ የእናቱም ስም ይኮልያ ነበር፤ የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች፡፡
4በሁሉም ነገር የአባቱን የአሜስያስ ምሳሌነት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር አደረገ፡፡
5እግዚአብሔርን መታዘዝ ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ለመፈለግ በልቡ ቆርጦ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር የተሳካለት አደረገው፡፡
6ዖዝያን ወጥቶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፡፡ የጌትንና የየብናንና የአዛጦንን የከተማ ቅጥሮች አፈረሰ፤ በአዛጦን አገርና በፍልስጤማውያን መካከል ከተሞችን ገነባ፡፡
7እግዚአብሔርም በፍልስጤማውያን ላይ፥ በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን ላይና በምዑናውያን ላይ ረዳው።
8አሞናውያንም ለዖዝያን ግብር ይከፍሉ ነበር፤ እጅግ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ዝናውም እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ወደ ሌሎች አገሮች ተሰራጨ።
9በተጨማሪም ዖዝያን በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በር፥ በሸለቆው በርና በቅጥሩ መዞሪያ ላይ ረጃጅም ማማዎችን ገንብቶ መሸጋቸው።
10በቆላው እንዲሁም በደጋው እጅግ ብዙ ከብቶች ስለነበሩት በምድረ በዳው የመጠባበቂያ ማማዎችን ሠራ፤ በርካታ ጉድጓዶችንም ቆፈረ። እርሻ ይወድ ስለነበርም በኮረብታማው አገርና በፍሬያማው መስክ ውስጥ ገበሬዎችና የወይን አትክልተኞች ነበሩት።
11በተጨማሪም ዖዝያን በጸሐፊው በይዒኤልና ከንጉሡ አለቆች በአንዱ በሐናንያ ሥልጣን ስር በነበረው በመዕሤያ በሚቆጠሩበት ቁጥር መሰረት የተደራጁ በቡድን ወደ ጦርነት ይሄዱ የነበሩ የተዋጊ ሰዎች ሠራዊት ነበሩት።
12የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የተዋጊ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።
13ከበታቻቸውም ንጉሡን ከጠላቱ ለመጠበቅ የሚረዳ በብርቱ ኃይል የሚዋጋ የሦስት መቶ ሰባት ሺህ እምስት መቶ ሰዎች ሠራዊት ነበር።
14ዖዝያንም ለሠራዊቱ ሁሉ ጋሻዎች፥ ጦሮች፥ የራስ ቁሮች፥ ጥሩሮች፥ ቀስቶችና የሚወነጭፉአቸውን ድንጋዮች አዘጋጅቶላቸው ነበር።
15በኢየሩሳሌምም ፍላጻዎችንና ትልልቅ ድንጋዮችን ለመወርወር በግንብና በመታኮሻ ቅጥር ላይ እንዲሆኑ የተካኑ ባለሙያዎች የፈለሰፏቸውን ማንቀሳቀሻ ሞተሮች ገነባ። እጅግ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በብዙ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ቦታዎች ተሰራጨ።
16ነገር ግን ዖዝያን በበረታ ጊዜ እስኪበላሽ ድረስ ልቡ ታበየ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን በማጠኑ አምላኩን እግዚአብሔርን በደለ።
17ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ደፋር ሰዎች የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለውት ገቡ።
18ንጉሡንም ዖዝያንን ተቃውመው፦"ዖዝያን ሆይ፦ ለእግዚአብሔር ዕጣን ማጠን ለእግዚአብሔር ለተቀደሱት ለካህናቱ ለአሮን ልጆች የተሰጠ እንጂ ዕጣን ማጠን ለአንተ አይደለም። ተላልፈሃልና ከቅዱሱ ቦታ ውጣ። በዚህ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ላንተ ምንም ክብር አይሆንልህም" አሉት።
19ዖዝያንም ተቆጣ። ዕጣን የሚያጥንበትን ጥና በእጁ ይዞ ነበር። በካህናቱ ላይ በተቆጣ ጊዜ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ በካህናቱ ፊት ግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት።
20ዋናው ካህንና ካህናቱ ሁሉ ተመለከቱት፤ እነሆ ግንባሩ ላይ ለምጻም ሆኖ ነበር። በፍጥነትም ከዚያ ቦታ አስወጡት። በእርግጥም እግዚአብሔር በለምጽ መትቶት ስለነበር እርሱም ለመውጣት ቸኮለ።
21ንጉሡም ዖዝያን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻም በመሆኑም ከእግዚአብሔር ቤት ተገልሎ ስለነበር ከሰዎች ርቆ በተለየ ቤት ይኖር ነበር። ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ የበላይ ሆኖ የምድሩን ሕዝብ ይገዛ ነበር።
22ዖዝያንን በተመለከተ ሌሎቹ ነገሮች የመጀመሪያውና የመጨረሻው የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ በጻፈው ውስጥ ይገኛሉ።
23ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ "ለምጻም ነው" ብለውም ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር ሥፍራ ቀበሩት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።