1አሜስያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፡፡ የኢየሩሳሌሟ እናቱ ስም ዮዓዳን ነበር፡፡
2በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹምና በተሰጠ ልብ አይደለም፡፡
3መንግሥቱ በሚገባ በጸናለት ጊዜ አባቱን ንጉሡን የገደሉትን አገልጋዮቹን ገደላቸው፡፡
4በሙሴ ሕግ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት፦"አባቶች ስለ ልጆች መሞት አይገባቸውም፤ ልጆችም ስለ አባቶች መሞት አይገባቸውም፡፡ ይልቁንም ማንኛውን ሰው ለራሱ ኃጢአት መሞት ይገባዋል" በማለት እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማድረግ የገዳዮቹን ልጆች አልገደለም፡፡
5በተጨማሪም አሜስያስ ይሁዳን በአንድነት ሰበሰበ፤ ይሁዳንና ቢንያምን ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች በታች መዘገባቸው፡፡ ከሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉትን ቆጠረ፤ ወደ ጦርነት ሊሄዱ የሚችሉ፥ ጋሻና ጦርም ሊይዙ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ፡፡
6ከእስራኤልም መቶ ሺህ ጦረኛ ሰዎች በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ፡፡
7ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ፦"ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር፥ ከኤፍሬምም ሰዎች ከአንዳቸውም ጋር አይደለምና የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር አይሂዱ፡፡
8ነገር ግን ብትሄድ በጦርነትም ደፋርና ብርቱ ብትሆን እግዚአብሔር በጠላት ፊት ይጥልሃል፤ ምክንያቱም የመርዳት ኃይል እና የመጣል ኃይል ያለው እግዚአብሔር ነው" አለው፡፡
9አሜስያስም ለእግዚአብሔር ሰው፦" ለእስራኤል ሠራዊት ስለሰጠሁት መቶ መክሊትስ ምን እናደርጋለን?" አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰውም፦ "እግዚአብሔር ከዚያ እጅግ የበለጠ ሊሰጥህ ይችላል" ብሎ መለሰለት፡፡
10በመሆኑም አሜስያስ ከኤፍሬም ወደርሱ የመጡትን ሠራዊት ለይቶአቸው እንደገና ወደ ቤት ላካቸው፡፡ ስለዚህም በይሁዳ ላይ ቁጣቸው እጅግ ነደደ፤ ወደ ቤትም በጋለ ቁጣ ተመለሱ፡፡
11አሜስያስም በርትቶ ሕዝቡን አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ መራቸው፤ በዚያም አሥር ሺህ የሴይርን ሰዎች ድል ነሳቸው፡፡
12የይሁዳም ሠራዊት አሥር ሺህ ሰዎች ከነሕይወታቸው ማርከው ወሰዱ፡፡ ወደ ኮረብታው ጫፍ ላይ ወሰዱአቸውና ሁሉም እስኪንኮታኮቱ ድረስ ከዚያ ወደ ታች ወረወሩአቸው፡፡
13ነገር ግን አሜስያስ ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያስመለሳቸው የሠራዊት ሰዎች ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን በይሁዳ ከተሞች ላይ ጥቃት አደረሱ፤ ከሕዝቡም ሦስት ሺህ ሰዎች መትተው እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ፡፡
14አሜስያስ የኤዶምያስን ሰዎች ገድሎ ከተመለሰ በኋላ የሴይርን ሰዎች ጣኦታት አምጥቶ የገዛ ራሱ አማልክት እንዲሆኑ አቆማቸው፡፡ በፊታቸውም ሰገደ፤ እጣንም አጠነላቸው፡፡
15ስለዚህም የእግዚአብሔር ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፡፡ አንድ ነቢይ ልኮ፦"የገዛ ሕዝባቸውን እንኳን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ለምን ፈለግሃቸው?" አለው፡፡
16ነቢዩም ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ እያለ ንጉሡ፦"የንጉሡ አማካሪ እንድትሆን አድርገንሃል? አቁም! ለምን መገደል ይገባሃል?" አለው፡፡ ነቢዩም ንግግሩን አቁሞ፦"ይህንን ድርጊት በመፈጸምህና ምክሬን ባለመስማትህ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንደወሰነ አውቃለሁ" አለ፡፡
17ከዚያም የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ፦" ና በጦርነት ፊት ለፊት እንጋጠም" ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ ላከ፡፡
18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ መልዕክተኞችን ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ መልሶ ላከና፦"በሊባኖስ የነበረ አንድ ኩርንችት፦ 'ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው' ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ መልዕክት ላከ፤ ነገር ግን አንድ የሊባኖስ አውሬ መንገድ ሲያልፍ ኩርንችቱን ረገጠው፡፡
19አንተም ፦'እነሆ ኤዶምያስን መትቻለሁ' ብለህ ልብህ ከፍ ከፍ ብሏል፡፡ በድልህ ኩራ፤ ነገር ግን በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተና ካንተ ጋር ይሁዳ ሁሉ ለምን በራስህ ላይ ችግር ፈጥረህ ትወድቃለህ?" አለው፡፡
20የይሁዳ ሰዎች ከኤዶምያስ አማልክት ምክር ከመፈለጋቸው የተነሳ የይሁዳን ሰዎች ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ ይህ ከእግዚአብሔር ታስቦ ነበርና አሜስያስ ሊሰማ አልፈለገም፡፡
21ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ ጥቃት አደረሰ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ የይሁዳ በነበረችው በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ፡፡
22ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደ ቤቱ ሸሸ፡፡
23የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ማረከው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞት መጣና ከኤፍሬም በር እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አራት መቶ ክንድ ርቀት ያህል አፈረሰው፡፡
24ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች በሙሉ እንዲሁም በንጉሡ ቤት የነበሩትን ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ከታገቱት ጋር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ፡፡
25የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ፥ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ፡፡
26አሜስያስን በተመለከተ ሌሎቹ ነገሮች የመጀመሪያውና የመጨረሻው እነሆ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፉ አይደለምን?
27አሜስያስም እግዚአብሔርን ከመከተል ከራቀበት ጊዜ አንስቶ በኢየሩሳሌም ሴራ ያሴሩበት ጀመር፡፡ ወደ ለኪሶም ሸሸ፤ ነገር ግን ከበስተኋላው ሰዎች ላኩበት፤ እነርሱም በዚያ ገደሉት፡፡
28በፈረስም ጭነው መልሰው አመጡት፤ በይሁዳም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፡፡