1በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ውጤት ያለው ነገር አደረገ፡፡ የመቶ አለቆቹን የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንን ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድን ልጅ ዓዛሪያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሴያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፡፡
2በይሁዳ ሁሉ ዞረውም ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን ቤቶች አባቶች መሪዎች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡
3ጉባኤውም ሁሉ ከንጉሡ ጋር በእግዚአብሔር ቤት ቃል ኪዳን አደረጉ፡፡ ዮዳሄም፦ "እነሆ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ዝርያዎች እንደተናገረው የንጉሡ ልጅ ይነግሣል" አላቸው፡፡
4"ማድረግ የሚገባችሁ ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ለማገልገል ከምትመጡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋውያን አንድ ሦስተኛው በበሮቹ ላይ ጠባቂዎች ትሆናላችሁ፡፡
5አንድ ሦስተኛችሁ ደግሞ በንጉሡ ቤት ትሆናላችሁ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ በመሠረቱ በር ላይ ይሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ላይ ይሁኑ፡፡
6ከካህናቱና ከሚያገለግሉት ሌዋውያን በስተቀር ማንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲገባ አትፍቀዱ፤ እነርሱ ለዛሬው ሥራቸው ተለይተው ተመድበዋልና መግባት ይገባቸዋል፡፡ ሁሉም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡
7ሁሉም ሰው የጦር መሣሪያውን በእጁ ይዞ ሌዋውያኑ ንጉሡን በሁሉም በኩል ሊከቡት ይገባቸዋል፡፡ ማንም ወደ ቤቱ ውስጥ ቢገባ ይገደል፡፡ ንጉሡም በሚገባበትና በሚወጣበት ጊዜ ሁሉ ከእርሱ ጋር ሁኑ፡፡
8በመሆኑም ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ በሁሉም መንገድ ካህኑ ዮዳሄ ባዘዘው መሠረት አገለገሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን በሰንበት ለማገልገል የሚገቡትንና በሰንበትም ከአገልግሎት ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ፤ ምክንያቱም ካህኑ ዮዳሄ የትኞቹንም የሥራ ክፍሎች አላሰናበተም ነበር፡፡
9ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የንጉሡን የዳዊትን ጦሮች፥ ትንንሽና ትልልቅ ጋሻዎች ለአለቆቹ አመጣላቸው፡፡
10ዮዳሄ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን እንደያዘ ከቤተ መቅደሱ ቀኝ በኩል እስከ ቤተ መቅደሱ ግራ በኩል በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ ንጉሡን እንዲከቡ ሁሉንም ወታደሮች በቦታቸው አቆማቸው፡፡
11ከዚያም የንጉሡን ልጅ አውጥተው፥ ዘውዱን በላዩ ላይ ደፍተው የቃል ኪዳኑ ሕግጋት የተጸፈበትን ጥቅልል ሰጡት፡፡ ከዚያም አነገሡት፤ ዮዳሄና ልጆቹም ቀቡት፡፡ ከዚያም ፦" ንጉሡ ረጅም ዘመን ይኑር!" ብለው ጮኹ፡፡
12ጎቶልያ የህዝቡን መሯሯጥና ንጉሡን ማወደስ ጫጫታ ስትሰማ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ሕዝቡ መጣች፡፡
13እነሆም ንጉሡ መግቢያው ላይ በራሱ ምሰሶ አጠገብ ቆሞ እንደነበርና አዛዦቹና መለከት ነፊዎቹ ከንጉሡ አጠገብ ቆመው እንደነበር አየች፡፡ የአገሩ ህዝብ ሁሉ ደስ እያላቸውና መለከት እየነፉ ነበር፡፡ ዘማሪዎቹም የሙዚቃ መሣሪያዎች እየተጫወቱ የውዳሴ መዝሙሮችን ይዘምሩ ነበር፡፡ ጎቶልያ ልብሷን ቀድዳ፦" አገር ከመክዳት የሚቆጠር ዓመፅ ነው! ዓመፅ ነው!" ብላ ጮኸች፡፡
14ካህኑ ዮዳሄ በሠራዊቱ ውስጥ መሪዎች የነበሩትን የመቶ አለቆች አውጥቶ፦ "ወደ ወታደሮቹ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል" አላቸው፡፡ ካህኑ ፦"በእግዚአብሔር ቤት አትግደሉአት" ብሎ ነበር፡፡
15በመሆኑም ገለል ብለው ሲያሳልፏት ወደ ንጉሡ ቤት ፈረሱ በር በሚወስደው መንገድ ሄደች፤ እዚያም ገደሏት፡፡
16ከዚያም ዮዳሄ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእርሱ፥ በሕዝቡና በንጉሡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፡፡
17ሕዝቡም ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፡፡ የበኣል መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፤ የበኣል ካህንን ማታንን በእነዚያ መሠዊያዎች ፊት ገደሉት፡፡
18ዮዳሄም በሙሴ ሕግ ተጽፎ እንደነበረው በእግዚአብሔር ቤት ከደስታና ከመዝሙር ጋር የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት ላይ የሾማቸው ሌዋውያን ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረት ከካህናቱ እጅ በታች እንዲያገለግሉ ለእግዚአብሔር ቤት ኃላፊዎችን ሾመ፡፡
19ርኩስ የሆነ ማንም በማናቸውም መንገድ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳይገባ በበሮቹ ላይ ጠባቂዎችን አኖረ፡፡
20ዮዳሄ ከእርሱ ጋር የመቶ አለቆቹን፥ ባላባቶቹን ፥ የሕዝቡን አስተዳዳሪዎችና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፡፡ ንጉሡንም በኮረብታ ላይ ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤት አወረደው፡፡ ሕዝቡም በላይኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጥተው ንጉሡን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡
21የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች፡፡ ጎቶልያንም በሰይፍ ገድለዋት ነበር፡፡