1ኢዮሳፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ከእነርሱ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ቦታ ነገሠ፡፡
2ኢዮራም የኢዮሳፍጥ ልጆች የሆኑ ወንድሞች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ነበሩት፡፡ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጆች ነበሩ፡፡
3አባታቸው ብዙ የብር፥ የወርቅ እና የሌሎች የከበሩ ነገሮች እንዲሁም በይሁዳም የተመሸጉ ከተሞችን ሰጣቸው፤ ዙፋኑን ግን የመጀመሪያ ልጁ ስለነበር ለኢዮራም ሰጠው፡፡
4ኢዮራም በአባቱ መንግሥት ላይ በወጣና ራሱን እንደ ንጉሥ አጽንቶ በመሠረተ ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉና የተለያዩ የእስራኤል ሌሎች መሪዎችን ጭምር በሰይፍ ገደላቸው፡፡
5ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፡፡
6የአክዓብን ሴት ልጅ አግብቶ ስለነበር የአክዓብ ቤት ያደርግ እንደነበር በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ የነበረውን ነገር አደረገ፡፡
7ነገር ግን እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ካደረገው ቃል ኪዳን የተነሳ የዳዊትን ቤት ለማጥፋት አልፈለገም፤ ለአርሱና ለዝርያዎቹ ሁልጊዜ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡
8በኢዮራም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ኃይል ላይ ዐመፀ፤ በራሳቸውም ላይ ንጉሥ ሾሙ፡፡
9በዚያን ጊዜ ኢዮራም ከአዛዦቹና ከሠረገላዎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እርሱንና የሠረገላዎቹን አዛዦች ከብበው የነበሩትን ኤዶማውያንን መታ፡፡
10በመሆኑም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ኤዶምያስ በይሁዳ ኃይል ላይ እንዳመፀ ነው፡፡ ኢዮራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለተወ የልብና ከተማ ጭምር በዚያው ጊዜ በኃይሉ ላይ ዐመጸ፡፡
11በተጨማሪም ኢዮራም በይሁዳ ተራራዎች ላይ መስገጃዎችን ሠርቶ ነበር፤ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎችም እንደ አመንዝራ ሌሎች አማልክትን እንዲከተሉ አደረጋቸው፡፡ በዚህ መንገድ ይሁዳን ከትክክለኛው መስመር አስወጣቸው፡፡
12ከነቢዩም ከኤልያስ አንድ ደብዳቤ ወደ ኢዮራም መጣለት፤ የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦" በአባትህ በኢዮሳፍጥ መንገድ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ ስላልሄድህ
13ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ስለሄድህ ይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች የአክዓብ ቤት እንዳደረገ እንደ አመንዝራ ሌሎች አማልክትን እንዲከተሉ ስላደረግሃቸው፤ በአባትህ ቤተሰብም ውስጥ ከአንተ የሚሻሉ የነበሩትን ወንድሞችህን በሰይፍ ስለገደልካቸው
14እነሆ እግዚአብሔር ሕዝብህን፥ ልጆችህን፥ ሚስቶችህን እና ሀብትህንም ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይመታል፡፡
15አንተም ራስህ ከበሽታው የተነሳ ከቀን ወደ ቀን አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ በአንጀትህ ሕመም እጅግ ትታመማለህ፡፡"
16እግዚአብሔርም የፍልስጤማውያንን እና በኢትዮጵያውያን አጠገብ ይኖሩ የነበሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሳበት፡፡
17እነርሱም ይሁዳን አጠቁ፤ ወረሩአትም፤ በንጉሡ ቤት ውስጥ የተገኘውን ሀብት ሁሉ ወሰዱ፤ ወንዶች ልጆቹንና ሚስቶቹንም ወሰዱ፡፡ ከታናሹ ልጁ ከአካዝያስ በስተቀር ምንም ልጅ አልቀረለትም፡፡
18ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን በማይችል በሽታ አንጀቱን መታው፤
19በተገቢው ጊዜ በሁለቱ ዓመት መጨረሻ ከሕመሙ የተነሳ አንጀቱ ወጣ፤ በብርቱ በሽታም ሞተ፡፡ ሕዝቡም ለእርሱ አባቶች እንዳደረገው ለክብሩ ምንም ችቦ አላበራም፡፡
20በሠላሳ ሁለት ዓመቱ ላይ መንገሥ ጀምሮ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሞተ፡፡ በነገሥታቱ መቃብር ሳይሆን በዳዊት ከተማ ቀበሩት፡፡