1ከዚህ ጊዜ በኋላ የሞዓብና የአሞን ሕዝቦች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሳፍጥን ሊዋጉት መጡ፡፡
2አንዳንድ ሰዎች መጥተው፦"ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው" ብለው ነገሩት፡፡
3ኢዮሳፍጥም ፈራ፤ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ራሱን አቀና፤ በመላው ይሁዳ ፆምን አወጀ፡፡
4ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ በአንድነት ተሰበሰበ፤ ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ፡፡
5ኢዮሳፍጥም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባዔ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፡፡
6"የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ አንተ በሰማይ ያለህ አምላክ አይደለህምን? በሕዝቦች ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዢ አይደለህምን? ኃይልና ብርታት በእጅህ ናቸው፤ በመሆኑም ማንም ሊቋቋምህ የሚችል የለም፡፡
7አምላካችን ሆይ በዚህ ምድር ላይ የነበሩትን ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ለዘላለም ለአብርሃም ዝርያዎች አልሰጠሃትምን?" አለ፡፡
8እነርሱም በውስጧ ኖሩባት፤
9"አደጋ/መቅሰፍት ቢመጣብን - ሰይፍ፥ ፍርድ፥ ወይም በሽታ፥ ወይም ረሃብ - (ስምህ በዚህ ቤት ስላለ) በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ እንቆምና በመከራችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ" በማለት ለስምህም ቅዱስ ሥፍራ በውስጥዋ ሠሩ፡፡
10አሁንም እነሆ እስራኤል ከግብጽ ምድር በሚወጡበት ጊዜ እንዲወሩዋቸው ያልፈቀድክላቸው ይልቁንም ዞር ብለው ያላጠፏቸው የአሞን፥ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሕዝቦች እዚህ ናቸው፤
11እነሆ ለወረታችን እንዴት እንደሚመልሱልን ተመልከት፤ እንድንወርሰው ከሰጠኸን ከምድርህ ሊያስወጡን መጥተዋል፡፡
12አምላካችን ሆይ አትፈርድባቸውምን? ይህንን ሊያጠቃን የመጣብንን ታላቅ ሠራዊት እንቋቋም ዘንድ ምንም ኃይል የለንም፡፡ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን በአንተ ላይ ናቸው" አለ፡፡
13ይሁዳ ሁሉ ከሕጻናቶቻቸው፥ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር፡፡
14በጉባዔው መካከል የእግዚአብሔር መንፈስ ከአሳፍ ልጆች አንዱ በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካርያስ ልጅ በየሕዚኤል ላይ መጣ፡፡
15የሕዚኤልም፦" ይሁዳ ሁሉ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እና ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ስሙ፤ እግዚአብሔር የሚላችሁ ይህ ነው፦"ከዚህ ታላቅ ሠራዊት የተነሳ አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ምክንያቱም ጦርነቱ የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለም፡፡
16ነገ በእነርሱ ላይ ለጦርነት ልትወጡ ይገባል፤ እነሆ በጺጽ መተላለፊያ መንገድ ይመጣሉ፡፡ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት በሸለቆው መጨረሻ ታገኙዋቸዋላችሁ፡፡
17በዚህ ጦርነት እናንተ መዋጋት የሚያስፈልጋችሁ አይደላችሁም፡፡ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ በቦታችሁ ቁሙ፤ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ለእናንተ የሚያደርገውን ማዳን ተመልከቱ፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ስለሆነ አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገ ለጦርነት ውጡባቸው" አለ፡፡
18ኢዮሳፍጥም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ፤ ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እግዚአብሔርን በማምለክ በፊቱ ወደቁ፡፡
19የቀዓትና የቆሬ ዝርያዎች ሌዋውያን የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በታላቅ ድምጽ ለማወደስ ቆመው ነበር፡፡
20ጥዋት በማለዳ ተነስተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ፡፡ እየሄዱም እያለ ኢዮሳፍጥ ቆሞ፦" ይሁዳና እናንተ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ድጋፍ ታገኛላችሁ፡፡ በነቢያቱም እመኑ፤ ይቃናላችኋልም" አለ፡፡
21ከሕዝቡ ጋር ከተማከረ በኋላም ከሠራዊቱ ፊት ቀድመው እየሄዱ "የቃል ኪዳን ታማኝነቱ ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ ለእግዚአብሔር ምሥጋናን ስጡ" በማለት ለእግዚአብሔር የሚዘምሩትንና ለቅዱስ ክብሩ ውዳሴ የሚሰጡትን ሾመ፡፡
22መዘመርና ማወደስ ሲጀምሩ ይሁዳን ሊዋጉ በመጡት በአሞን፥ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦር አስነስቶ በድንገት እንዲያጠቋቸው አደረገ፡፡ እነርሱም ተሸነፉ፡፡
23የአሞንና የሞዓብ ሰዎች የሴይርን ተራራ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ እስኪገድሉዋቸውና እስኪያጠፏቸው ድረስ ሊዋጉዋቸው ተነስተው ነበር፡፡ የሴይርን ተራራ ነዋሪዎች በጨረሷቸው ጊዜ ሁሉም እርስ በእርስ ለመጠፋፋት ተረዳዱ፡፡
24ይሁዳ ምድረ በዳውን ወደሚመለከቱበት ቦታ ሲመጡ ሠራዊቱን ተመለከቱ፡፡ እነሆ ሞተው በምድሩም ላይ ወድቀው ነበር፤ አንድም ያመለጠ ሰው አልነበረም፡፡
25ኢዮሳፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ለመውሰድ በመጡ ጊዜ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ የተትረፈረፈ ባለጸግነትና የከበሩ ጌጦች አገኙ፤ ለራሳቸውም በዘበዙ፡፡ እጅግ ብዙ ስለነበርም ምርኮውን ለመውሰድ ሦስት ቀናት ፈጀባቸው፡፡
26በአራተኛው ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፡፡ በዚያም እግዚአብሔርን አወደሱ፤ ስለዚህም የዚያ ሥፍራ ስም እስከዛሬ ድረስ "የበረከት ሸለቆ" ነው፡፡
27የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቷቸዋልና በደስታ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ኢዮሳፍጥ እየመራቸው ተመለሱ፡፡
28በበገናና በመሰንቆ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ እግዚአብሔር ቤት መጡ፡፡
29እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደተዋጋ በሰሙ ጊዜ በሕዝቦች ነገሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ፡፡
30በመሆኑም አምላኩ በዙሪያው ሁሉ ሰላም ስለሰጠው የኢዮሳፍጥ መንግሥት ጸጥታ ሰፈነባት፡፡
31ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ፡፡ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ሠላሳ አምስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ለሃያ አምስት ዓመታት ነገሠ፡፡ የእናቱ የሺልሒ ሴት ልጅ ስም ዓዙባ ነበር፡፡
32በአባቱም በዓሳ መንገዶች ሄደ፤ ከእነርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን የነበረውን ነገር አደረገ፡፡
33ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች ገና አልተወገዱም ነበር፡፡ ሕዝቡም ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ ገና አላቀኑም ነበር፡፡
34ኢዮሳፍጥን በተመለከተ ሌሎቹ ጉዳዮች የመጀመሪያውና የመጨረሻው በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ እንደተመዘገበው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ውስጥ ተጽፈዋል፡፡
35ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ እጅግ ክፋት ከፈጸመው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ራሱን አዛመደ፡፡
36በባህር ላይ የሚሄዱ መርከቦችን ለመገንባት ከእርሱ ጋር ተባበረ፡፡ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር ገነቡ፡፡
37የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር ፦" ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራዎችህን አፍርሷል፤" ብሎ በኢዮሳፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረበት፡፡ መርከቦቹም ተሰባበሩ፤ ጉዞ ለማድረግም አልቻሉም፡፡