1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥም ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደህና ተመለሰ፡፡
2ያኔ የባለ ራዕዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፤ ንጉሡንም ኢዮሳፍጥን፦"ክፉውን ልትረዳ ይገባሃልን? እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ልትወድ ይገባሃልን? ለዚህ ድርጊትህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል፡፡
3ነገር ግን የማምለኪያ አፀዶቹን ከምድሪቱ ላይ አስወግደሃልና እግዚአብሔርን ለመፈለግ ቆርጠህ ልብህን አዘጋጅተሃልና በአንተ ዘንድ መልካምነት ተገኝቶብሃል" አለው፡፡
4ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ከቤርሳቤህ እስከ ተራራማው የኤፍሬም አገር ድረስ እንደገና በሕዝቡ መካከል ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ መለሳቸው፡፡
5በምድሪቱ ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆችን አስቀመጠ፡፡
6ፈራጆቹንም፦"የምትፈርዱት ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው ስላልሆነ ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ አጢኑ፤ በፍርድ ነገር እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤
7አሁንም የእግዚአብሔር ፍርሃት በእናንተ ላይ ይሁን፡፡ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ምንም በደል የለምና፤ ለሰው ፊት ማድላት ወይም መማለጃ መውሰድ የለምና በምትፈርዱበት ጊዜ ተጠንቀቁ" አላቸው፡፡
8በተጨማሪም ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም ከሌዋውያኑንና ከካህናቱ የተወሰኑትንና ከእስራኤል የአባቶች ቤቶች መሪዎች የተወሰኑትን የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲያስፈጽሙና ጠቦችን እንዲፈቱ ሾማቸው፡፡ እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፡፡
9"እግዚአብሔርን በመፍራት፥ በታማኝነትና በፍጹም ልብ የምታደርጉት ይህ ነው፤
10በደም መፍሰስ ጉዳይ ቢሆን፥ በሕግና በትእዛዝ፥ በሥርዓት ወይም በድንጋጌ ጉዳዮች ቢሆን በከተሞቻቸው ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ ምንም ኣይነት ጠብ ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቁጣ በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይወርድ ልታስጠነቅቋቸው ይገባል፡፡ እንደዚህ ብታደርጉ በኃጢአት በደለኛ አትሆኑም፡፡
11እነሆ ለእግዚአብሔር በሚሆኑት ነገሮች ሁሉ ላይ ሊቀ ካህናቱ አማርያ፥ በንጉሡ ጉዳዮች ሁሉ ላይ የተሾመው የይሁዳ ቤት መሪ የእስማኤል ልጅ ዝባድያ አለቆች ናቸው፡፡ ሌዋውያኑም ደግሞ የሚያገለግሏችሁ ባለሥልጣናት ይሆናሉ፡፡ በድፍረት አድርጉ፤ እግዚአብሔርም መልካም ከሆኑት ጋር ይሁን፡፡