1ኢዮሣፍጥ ታላቅ ባለጠግነትና ክብር ነበረው፡፡ ከቤተሰቦቹ አንዱ ሴት ልጁን እንዲያገባ በማድረግ ከአክዓብ ጋር ራሱን አዛመደ፡፡
2ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ፡፡ አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ በርካታ በጎችንና በሬዎችን አረደላቸው፡፡ ከእርሱም ጋር ሬማት ዘገለአድን ለማጥቃት ይሄድ ዘንድም አክዓብ አሳመነው፡፡
3የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ፦ "ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለአድ ትሄዳለህን?" አለው፡፡ ኢዮሣፍጥም ፦"እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በጦርነቱ ውስጥ ካንተ ጋር አብረን እንሆናለን" ብሎ መለሰለት፡፡
4ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ ፦ "እባክህን ለመልስህ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል ጠይቅ" አለው፡፡
5ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ፦ "ወደ ሬማት ዘገለአድ ለጦርነት መሄድ ይገባናል ወይስ መሄድ አይገባኝም?" አላቸው፡፡ እነርሱም ፦" እግዚአብሔር ለንጉሡ ድል ይሰጠዋልና አጥቃት!" አሉት፡፡
6ኢዮሣፍጥ ግን፦ "ምክር የምንጠይቀው አሁንም ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሰው በእዚህ የለምን?" አለ፡፡
7የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ፦" የእግዚአብሔርን ምክር የምንጠይቅበት አሁንም አንድ ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ አለ፤ ነገር ግን ችግር ብቻ እንጂ ስለእኔ ምንም ነገር መልካም ትንቢት ከቶም ተናግሮልኝ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ" አለው፡፡ኢዮሣፍጥ ግን ፦ "ንጉሥ እንደዚያ አይበል" አለ፡፡
8ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ አንድ ሹም ጠርቶ ፦"የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው" ሲል አዘዘው፡፡
9የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የአስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥ መጎናጸፊያቸውን እንደለበሱ እያንዳንዳቸው በዙፋን ላይ በሰማርያ በር መግቢያ በግልጽ ሥፍራ ላይ ተቀምጠው ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት እየተናገሩ ነበር፡፡
10የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም ለራሱ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 'በእነዚህ ቀንዶች አርመናውያን እስኪያልቁ ድረስ ትወጋቸዋለህ'" አለ፡፡
11ነቢያቱም ሁሉ፦" እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ስለሚሰጣት ሬማት ዘገለዓድን አጥቃና አሸንፍ" እያሉ ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡
12ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልዕክተኛ ፦" እነሆ የነቢያቱ ቃላት በአንድ አፍ ለንጉሡ መልካም ነገሮች ያውጃሉ፡፡ እባክህን ያንተም ቃል ከእነርሱ የአንዱን ቃል ዓይነት ይሁንና መልካም ነገሮች ተናገር" ሲል ተናገረው፡፡
13ሚክያስም፦"ሕያው እግዚአብሔርን የምናገረው አምላኬ እርሱ የሚለውን ነው" ብሎ መለሰ፡፡
14ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦" ሚክያስ ሆይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት መሄድ ይገባናል ወይስ መቅረት?"አለው፡፡ ሚክያስም፦" አጥቃና አሸንፍ! ታላቅ ድል ይሆንልሃልና!" ብሎ መለሰለት፡፡
15ከዚያም ንጉሡ ፦" በእግዚአብሔር ስም ከእውነቱ በቀር ሌላ ምንም ነገር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ እንድትምል ላደርግህ ይገባኛል?" አለው፡፡
16ሚክያስም፦" እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየኋቸው፤ እግዚአብሔርም፦ 'እነዚህ እረኛ የላቸውም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ' አለ" ብሎ ተናገረ፡፡
17በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ለኢዮሳፍጥ ፦" እኔን በተመለከተ ጥፋት ብቻ እንጂ መልካም ትንቢት እንደማይናገርልኝ አልነገርኩምን?" አለው፡፡
18ከዚያም ሚክያስ፦" እንግዲህ ሁላችሁም የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው እንደነበር አየሁ፡፡
19እግዚአብሔርም ፦" የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ወደ ሬማት ዘገለዓድ እንዲወጣና እንዲወድቅ የሚያታልለው ማነው?" አለ፡፡ አንዱ በእዚህ መንገድ ብሎ ሲመልስ ሌላውም በዚያ መንገድ ብሎ መለሰ፡፡
20ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፦" እኔ አታልለዋለሁ" አለ፡፡ እግዚአብሔርም ፦"እንዴት?" አለው፡፡
21መንፈሱም፡-" ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ" አለ፡፡ እግዚአብሔርም፦" ታታልለዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ አሁንም ሂድና እንደዚሁ አድርግ" ብሎ መለሰ፡፡
22አሁንም እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አስቀምጧል፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንዲመጣብህ ተናግሯል፡፡
23የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም ቀረብ ብሎ ሚክያስን በጥፊ መታውና ፦"የእግዚአብሔር መንፈስ ለአንተ ሊናገር በየትኛው መንገድ ከእኔ ሄደ?" አለው፡፡
24ሚክያስም፦" እነሆ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ አንድ የውስጥ ክፍል ስትሸሽ ታውቀዋለህ" አለው፡፡
25የእስራኤል ንጉሥም ለአገልጋዮቹ ፦" እናንተ ሰዎች ሚክያስን ያዙና ወደ ከተማይቱ አስተዳዳሪ ወደ አሞንና ወደ ልጄ ወደ ኢዮአስ ውሰዱት፤"
26ንጉሡ፦' በደህና እስከምመለስ ድረስ ይህንን ሰው እስር ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ጥቂት ምግብ ብቻ እና ጥቂት ውሃ ብቻ መግቡት' ይላል በሉት" አላቸው፡፡
27ሚክያስም፦" አንተ በደህና ከተመለስህ በእኔ የተናገረው እግዚአብሔር አይደለም" አለ፡፡ ጨምሮም፦"እናንተ ሕዝብ ሁሉ ይህንን ስሙ" አለ፡፡
28በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ሬማት ዘገለዓድን ሊዋጉ ወጡ፡፡
29የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን፡-"እኔ እንዳልታወቅ አለባበሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ንጉሣዊ መጎናፊያህን ልበስ" አለው፡፡ በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ በአለባበሱ እንዳይታወቅ ራሱን ለውጦ ወደ ጦርነቱ ሄዱ፡፡
30የአራምም ንጉሥ የሰረገሎቹን አዛዦች፦ "ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ወታደሮችን እንዳታጠቁ፤ ይልቁንም የእስራኤል ንጉሥን ብቻ አጥቁ" በማለት አዝዟቸው ነበር፡፡
31የሰረገሎቹ አለቆች ኢዮሳፍጥን ባዩ ጊዜ፦"የእስራኤል ንጉሥ ያ ነው ፤" አሉ፡፡ ሊያጠቁትም ወደ እርሱ ዞሩበት፤ ነገር ግን ኢዮሳፍጥ ሲጮህ እግዚአብሔር ረዳው፡፡ እግዚአብሔርም ከእርሱ ዞር አደረጋቸው፡፡
32የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልነበረ ባዩ ጊዜ እርሱን ከመከታተል ተመለሱ፡፡
33አንድ ሰው ግን በዘፈቀደ ቀስቱን ሲስበው የእስራኤል ንጉሥን በጥሩር መገጣጠሚያዎቹ መካከል ወጋው፡፡ ያን ጊዜ አክዓብ የሰረገላውን ነጂ፦" ክፉኛ ተወግቻለሁና አቅጣጫህን ቀይርና ከጦርነቱ ውስጥ አውጣኝ፡፡
34በዚያን ጊዜ ጦርነቱ እጅግ የከፋ ሆነ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አርመናውያንን እየተመለከተ እስኪመሽ ድረስ ሰረገላውን እንደተደገፈ ነበር፡፡ ፀሐይ በምታዘቀዝቅበት ጊዜ አካባቢ ሞተ፡፡