1ልጁ ኢዮሳፍጥ በእርሱ ቦታ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ራሱን አጠነከረ፡፡
2በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አስቀመጠ፤ በይሁዳም ምድር እና አባቱ አሳ በያዛቸው የኤፍሬም ከተሞች ውስጥ የጦር ሠፈር አደራጀ፡፡
3በአባቱ በዳዊት በፊተኛይቱ መንገድ ስለሄደና በአሊምንም ስላልፈለገ እግዚአብሔር ከኢዮሣፍጥ ጋር ነበረ፡፡
4በዚያ ፈንታ በአባቱ አምላክ ላይ ተደገፈ፤ እንደ እስራኤል ባህርይ ሳይሆን በአምላኩ ትዕዛዛት መሠረት ሄደ፡፡
5በመሆኑም እግዚአብሔር መንግሥቱን በእጁ አጸናለት፤ ይሁዳ ሁሉ ለኢዮሣፍጥ ግብር ያመጡለት ነበር፡፡ የተትረፈረፈ ባለጠግነትና ክብርም ነበረው፡፡
6ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ የጸና ነበረ፡፡ መስገጃዎቹንና የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ከይሁዳ አስወገደ፡፡
7በነገሠም በሦስተኛው ዓመት ያስተምሩ ዘንድ ባለሥልጣናቱን ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልንና ሚኪያስን ወደ ይሁዳ ከተሞች ላካቸው፡፡
8ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ ሸማያ፥ነታንያ፥ ዝባድያ፥ አሣኤል፥ ሰሚራሞት፥ዮናትን፥ አዶንያስ፥ ጦብያ እና ጠባዶንያ ነበሩ፡፡ ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ኤሊሳማና ኢዮራም ነበሩ፡፡
9እነርሱም የእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ከእነርሱ ጋር ስለነበር በይሁዳ አስተማሩ፡፡በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ተዘዋውረው በሕዝቡ መካከል አስተማሩ፡፡
10በይሁዳ ዙሪያ በነበሩት አገራት ነገሥታት ላይ የእግዚአብሔር ድንጋጤ ስለወደቀባቸው ከኢዮሣፍጥ ጋር ምንም ጦርነት አላደረጉም፡፡
11የተወሰኑት ፍልስጤማውያን ለኢዮሳፍጥ ስጦታዎችና ብር እንደ ግብር ያመጡለት ነበር፡፡ አረቦችም ሰባት ሺህ ሰባት መቶ የአውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ የፍየሎች መንጋዎችን አመጡለት፡፡
12ኢዮሣፍጥም እጅግ ብርቱ ሆነ፤ በይሁዳም ትልልቅ ምሽጎችንና የመጋዘን ከተሞችን ሠራ፡፡
13በይሁዳም ከተሞች በርካታ አቅርቦት እና በኢየሩሳሌምም ጠንካራና ደፋር ሰዎች - ወታደሮች ነበሩት፡፡
14በአባቶቻቸው ቤቶች ስም ቅደም ተከተል ዝርዝራቸው ይህ ነው፤ ከይሁዳ የሺዎች አዣዦች፥ አዣዡ ዓድና ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ተዋጊ ሰዎች፤
15ከእርሱም ቀጥሎ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
16ከእርሱም ቀጥሎ ራሱን በፈቃዱ እግዚአብሔርን ለማገልገል ያቀረበ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ተዋጊ ሰዎች ነበሩ፤
17ከቢኒያም ኃይለኛ ደፋር ሰው የነበረው ኤሊዳሄ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ተዋጊ ሰዎች ነበሩ፤
18ከእርሱም ቀጥሎ ዮዛባት ከእርሱም ጋር ለጦርነት የተዘጋጁ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤
19ንጉሡ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካስቀመጣቸው በተጨማሪ እነዚህ ንጉሡን የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡