1አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ የጠብ ጫሪነት ድርጊት ፈጸመ፡፡ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ምድር ማንም መውጣትና መግባት እንዳይፈቀድለት ራማን ዙሪያዋን ሠራ፡፡
2አሳም ከእግዚአብሔር ቤት እና ከንጉሡ ቤት መጋዘኖች ብርና ወርቅ አውጥቶ በደማስቆ ይኖር ወደ ነበረው ወደ አራም ንጉሥ ወደ ቤንሃዳድ ላከው፡፡
3"በአባትህና በአባቴ መካከል እንደነበረው በእኔና በአንተ መካከል የሰላም ስምምነት ይኑር፡፡ እነሆ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ፤ ከእኔ ርቆ እንዲተወኝ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያደረግኸውን የሰላም ስምምነት አፍርስ" አለው፡፡
4ቤንሃዳድም ንጉሡን አሳን ሰማው፤ የእስራኤልን ከተሞች እንዲያጠቁም የሠራዊቱን አለቆች ላከ፡፡ እነርሱም ኦዮንን፥ ዳንን፥ አቤልማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ መቱ፡፡
5ባኦስም ይህንን ሲሰማ የራማን ዙሪያዋን መሥራቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ፡፡
6በዚያን ጊዜ ንጉሡ አሳ ይሁዳን ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ከተማይቱን ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋዮችና ጣውላዎች ወሰዱ፡፡ ከዚያም ንጉሡ አሳ ያንን የግንባታ ዕቃ ጌባንና ምጽጳን ለመሥራት ተጠቀመበት፡፡
7በዚያን ጊዜ ባለ ራዕዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ሄዶ፦ "በአራም ንጉሥ ስለታመንህና በአምላክህ በእግዚአብሔር ስላልታመንህ የአራም ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል፡፡
8እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሯቸው ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ታላቅ ሠራዊት አልነበሩምን? ነገር ግን በእግዚአብሔር ስለታመንህ በእነርሱ ላይ ድልን ሰጠህ፡፡
9ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የተሰጠ የሆነውን ሰው በኃይሉ ያበረታ ዘንድ የእግዚአብሔር ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይዘዋወራሉ፡፡ ነገር ግን አንተ በዚህ ጉዳይ ስንፍና አድርገሃል፡፡ ከአሁን ጊዜ ጀምሮ ጦርነት ይሆንብሃል" አለው፡፡
10በዚያን ጊዜ ንጉሡ አሳ በባለ ራዕዩ ላይ ተቆጣ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቆጥቶ ስለነበር እስር ቤት ውስጥ አኖረው፡፡ በዚያው ጊዜ አሳ ከሕዝቡ የተወሰኑትን አስጨነቀ፡፡
11እነሆ የአሳ ድርጊቶች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እነሆ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፡፡
12አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠኝ ዓመቱ እግሩን ታመመ፤ ሕመሙም እጅግ ጽኑ ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ከባለ መድኃኒቶች ብቻ እንጂ ከእግዚአብሔር እርዳታ አልፈለገም፡፡
13አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ፡፡
14በዳዊት ከተማ ለእርሱ ለራሱ በቆፈረው በራሱ መቃብር ቀበሩት፡፡ በተካኑ ቀማሚዎች በተሰናዳ ልዩ ልዩ የቅመም ዓይነቶች በጣፋጭ መዓዛ በተሞላ ቃሬዛ ላይ አኖሩት፡፡ ለክብሩም እጅግም ታላቅ የሆነ እሳት ለኮሱለት፡፡