1የእግዚአብሔር መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ መጣ፡፡
2አሳንም ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፦ "አሳ፥ ይሁዳ ሁሉና ቢኒያም ሆይ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፡፡ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል፡፡
3እስራኤል ለረጅም ጊዜ ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪ ካህን እና ያለ ሕግ ይኖሩ ነበር፡፡
4በጭንቃቸው ጊዜ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ሲፈልጉት ይገኝላቸው ነበር፡፡
5በዚያን ዘመን ርቆ ለሚሄደውና ወደዚህ ቅርብ ለሚመጣው ሰላም አልነበረም፤ ይልቁንም በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ታላቅ ጭንቅ ነበር፡፡
6እግዚአብሔር በሁሉም ዓይነት መከራዎች ያስጨንቃቸው ስለነበር ፍርስርሳቸው ወጥቶ ነበር፤ ህዝብ ከህዝብ ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር፡፡
7እናንተ ግን ሥራችሁ ብድራት ስለአለው በርቱ እጃችሁም እንዲደክም አትፍቀዱ፡፡"
8ይህንን ቃል፥ የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ብርታት አግኝቶ ከይሁዳና ከቢኒያም ምድር ሁሉ፥ ከተራራማው የኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት መተላለፊያ ፊት ለፊት የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ እንደገና ሠራ፡፡
9ይሁዳንና ቢኒያምን ሁሉ ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም ወገን የሆኑትን ከእርሱም ጋር የዘለቁትን ሰበሰበ፡፡ እግዚአብሔር አምላኩ ከእርሱ ጋር እንደነበር ሲያዩ ከእስራኤል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ እርሱ መጡ፡፡
10በመሆኑም አሳ በነገሠ በአስራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡
11በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ የተወሰነውን ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎችና ፍየሎች ለእግዚአብሔር ሠዉ፡፡
12የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው ሊፈልጉት ቃል ኪዳን አደረጉ፡፡
13የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ ማንም ቢኖር ሰውየው ታናሽ ይሁን ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ሊገደል እንደሚገባው ተስማሙ፡፡
14በታላቅ ድምጽና በጩኸት፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ለእግዚአብሔር ማሉ፡፡
15በሙሉ ልባቸው መሐላውን ስለፈጸሙ፥ እግዚአብሔርንም በሙሉ ፍላጎታቸው ስለፈለጉት እርሱም ተገኝቶላቸው ስለነበር ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር በዙሪያቸው ሁሉ ሰላምን ሰጣቸው፡፡
16ንጉሡም አሳ ሴት አያቱ መዓካ ከማምለኪያ አጸድ አስጸያፊ ምስል/ጣኦት ስላበጀች ከንግሥትነትዋ አስወገዳት፡፡ አሳም አስጸያፊ ምስሏን/ጣኦቷን ቆርጦ አቧራ አድርጎ ፈጨው፤ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው፡፡
17መስገጃዎቹ ግን ከእስራኤል አልራቁም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ታማኝና ታዛዥ ነበር፡፡
18የእግዚአብሔር የሆኑትን የአባቱን ነገሮችና የገዛ ራሱን ነገሮች፥ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት ውስጥ አስገባቸው፡፡
19አሳም እስከነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ከዚያ ወዲያ ጦርነት አልነበረም፡፡