መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሁለተኛ ዜና 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜና እርሱም በበረታበት በዚያን ጊዜ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ፡፡
2ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኞች ባለመሆናቸው ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊያጠቃ መጣባት፡፡
3ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ከስልሳ ሺህ ፈረሰኞች ጋር መጠባት፡፡ ከእርሱም ጋር ሊቆጠሩ የማይችሉ ወታደሮች ሊቢያውያን፥ ሱካውያን እና ኢትዮጵያውያን መጡ፡፡
4የይሁዳ ይዞታ የነበሩትን የተመሸጉ ከተሞች ወሰደና ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡
5ይሄኔ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ የተነሳ ወደ ኢየሩሳሌም በአንድነት ወደተሰበሰቡት መሪዎች መጣ፡፡ ሸማያ እንዲህ አላቸው፦ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ ለሺሻቅ እጅ አሳልፌ ሰጠኋችሁ፡፡"
6በዚያን ጊዜ የእስራኤል መሳፍንትና ንጉሡ ራሳቸውን አዋረዱ፤ "እግዚአብሔር ጻድቅ ነው" አሉ፡፡
7እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሽማያ መጣ፦ "ሰውነታቸውን አዋርደዋል፡፡ አላጠፋቸውም፤ በተወሰነ ደረጃ አድናቸዋለሁ፡፡ ቁጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፡፡
8ነገር ግን እኔን ማገልገል እና የሌሎች አገራትን ገዢዎች ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባቸው አገልጋዮቹ ይሆናሉ" አለ፡፡
9ስለሆነም የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊያጠቃ መጥቶ የእግዚአብሔርን ቤት የከበሩ መዝገቦችና የንጉሡን ቤት የከበሩ መዝገቦች ወሰደ፡፡ ሁሉንም ነገር ወሰደ፤ ሰለሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎችም ጭምር ወሰደ፡፡
10ንጉሥ ሮብዓም በእነርሱ ምትክ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የንጉሡን ቤት በሮች በሚጠብቁት ዘበኞች አለቃዎች እጅ አስቀመጣቸው፡፡
11ከዚያ በኋላ ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቁጥር ዘበኞቹ ይሸከሙአቸው ነበር፤ ከዚያም ወደ ዘበኞቹ ቤት ይመልሷቸው ነበር፡፡
12ሮብዓም ሰውነቱን ባዋረደ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳያጠፋው የእግዚአብሔር ቁጣ ከእርሱ ተመለሰ፤ ደግሞም በይሁዳ የተወሰነ መልካምነት ገና ይገኝ ነበር፡፡
13ንጉሡም ሮብዓም ንግሥናውን በኢየሩሳሌም አጠናከረ፤ በዚህ ሁኔታም ገዛ፡፡ ሮብዓም መንገሥ ሲጀምር አርባ አንድ ዓመቱ ነበር፤ እግዚአብሔር ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ አስራ ሰባት ዓመታት ነገሠ፡፡ የአሞናዊቷ እናቱም ስም ናዕማ ነበር፡፡
14እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉውን ነገር አደረገ፡፡
15ሮብዓምን የሚመለከቱ ሌሎች ነገሮች የመጀመሪያውና የመጨረሻው የትውልዶች ስም ዝርዝርና በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የነበሩት ያልተቋረጡ ጦርነቶች በተመዘገቡበት በነቢዩ ሸማያና በባለ ራዕዩ በአዶ ጽሑፎች ውስጥ የተጻፉ አይደለምን?
16ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ቦታ ነገሠ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።