1በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፣ እንዴት መመላለስና እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንዳለባችሁ ከእኛ በተቀበላችሁት ትምህርት መሠረት አሁን እንደምትኖሩት ሁሉ ከዚህም አብልጣችሁ እንድታደርጉ በጌታ በኢየሱስ እንመክራችኋለን እናደፋፍራችሁማለን።
2በጌታ በኢየሱስ በኩል እንዴት ያለውን ትዕዛዝ እንደሰጠናችሁ ታውቃላችሁና፤
3በቅድስና መኖራችሁ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፣
4ከእናንተ እያንዳንዱ ከዝሙት በመራቅ የራሱን አካል በቅድስናና በክብር ማግኘት እንዳለበት ታውቃላችሁ፣
5እግዚአብሔርን እንደማያውቁ እንደ አሕዛብ የፍትወት ምኞት አይሁን፣
6በዚህ ጉዳይ ማንም አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል፣ ምክንያቱም አስቀድመን እንደነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ ስለነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚበቀል ነውና።
7እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለእርኩሰት አልጠራንም።
8ስለዚህ ይህንን የማይቀበል ሰውን ሳይሆን የማይቀበለው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን ነው።
9የወንድማማች መዋደድን በተመለከተ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፣ እርስ በርስ ስለመዋደድ እናንተው ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና።
10በመቄዶንያ ላሉ ወንድሞች ሁሉ ይህንን ታደርጋላችሁ፣ ይሁን እንጂ ወንድሞች ሆይ፣ ከዚህም አብልጣችሁ እንድታደርጉት ደግሞ እንመክራችኋለን።
11ደግሞም ልክ እንዳዘዝናችሁ በጸጥታ እንድትኖሩ፣ በራሳችሁ ጉዳይ ላይ እንድታተኩሩና በገዛ እጆቻችሁ እንድትሠሩ እንመክራችኋለን።
12በማያምኑት ዘንድ በአግባብ እንድትመላለሱና በኑሮአችሁ ምንም የሚጎድላችሁ እንዳይኖር ይህንን አድርጉ።
13ወንድሞች ሆይ፣አንቀላፍተው ስላሉት ባለማወቃችሁ ስለወደፊቱ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሀዘናችሁ መሪር እንዲሆን አንፈልግም።
14ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ ካመንን በእርሱ አምነው ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ጋር ያመጣቸዋል።
15በጌታ ቃል የምንነግራችሁ ይህንን ነው፣ ጌታ በሚመጣበት ጊዜ እኛ ሕያዋን ሆነን የቀረነው አስቀድመው ያንቀላፉትን በርግጥ አንቀድምም።
16ጌታ ራሱ በታላቅ ድምፅ፣ በመላዕክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር መለከት ከሰማይ ይወርዳል፣ በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሳሉ።
17ከዚያም እኛ ሕያዋን ሆነን የምንገኘው ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፣ ሁልጊዜም ከጌታ ጋር እንሆናለን።
18ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በእነዚህ ቃላት ተጽናኑ።