1ወንድሞች ሆይ፣ አሁን ስለ ጊዜያትና ዘመናት ሊጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም።
2ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ የጌታ ቀንም እንደዚያው እንደሆነ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁና።
3እርጉዝን ሴት የምጥ ህመም እንደሚሆንባት ሁሉ “ሁሉ ሰላምና ደህና ነው” በሚሉበት በዚያን ጊዜ ድንገተኛ ጥፋት ይመጣባቸዋል፣ እነርሱም በምንም መንገድ አያመልጡም።
4ወንድሞች ሆይ፣ እናንተ ግን ያ ቀን እንደ ሌባ ይመጣባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም።
5ሁላችሁም የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ልጆች አይደለንም።
6እንግዲያውስ ሌሎች እንደሚያደርጉት አናንቀላፋ፣ ነገር ግን እንንቃ በመጠንም እንኑር።
7የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉ፣ የሚሰክሩትም በሌሊት ይሰክራሉና።
8የብርሃን ልጆች እንደመሆናችን በመጠን እንኑር፣ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር፣ የድነታችንን ተስፋ እርግጠኝነትም እንደ ራስ ቁር እንልበስ።
9በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድነትን ልንቀበል እንጂ እግዚአብሔር ለቁጣ አልመደበንም፣
10የነቃን ወይም ያንቀላፋን ብንሆን ከእርሱ ጋር እንድንኖር ስለ እኛ ሞቶአልና።
11ስለዚህ አሁን እንደምታደርጉት ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ፣ አንዱም ሌላውን ያንጸው።
12ወንድሞች ሆይ፣በመካከላችሁ በማገልገል የሚለፉትንና በጌታ የሚያስተዳድሯችሁን፣ የሚመክሯችሁንም እንድታከብሯቸው እንጠይቃችኋለን።
13ደግሞም በሥራቸው ምክንያት ከፍ ያለ የፍቅር አክብሮት እንድታሳዩአቸው እንጠይቃችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ኑሩ።
14ወንድሞች ሆይ እንመክራችኋለን፣ ያለ ሥርዓት የሚመላለሱትን ገስጹአቸው፣ ድፍረት ያጡትን አበረታቱአቸው፣ ደካሞችን ደግፉአቸው፣ሰውን ሁሉ ታገሱ።
15ማንም ስለተደረገበት ክፉ ነገር ለሌላው በክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፣ ነገር ግን ለእርስ በርሳችሁና ለሰው ሁሉ መልካም የሆነውን ለማድረግ ሁልጊዜ ትጉ።
16ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፣
17ባለማቋረጥ ጸልዩ፣
18ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ፣ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ነውና።
19የመንፈስ ቅዱስን ሥራ አታዳፍኑ።
20ትንቢትን አትናቁ።
21ሁሉን መርምሩ፣ መልካም የሆነውን ያዙ፣
22ማንኛውንም ዓይነት ክፋት አስወግዱ።
23የሰላም አምላክ ራሱ ፈጽሞ ይቀድሳችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ መላው መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ ያለ ነቀፋ ይጠበቅ።
24የጠራችሁ ታማኝ ነው፣ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።
25ወንድሞች ሆይ፣ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ።
26ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው።
27ይህ መልዕክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ።
28የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።