1ወንድሞች ሆይ! ወደ እናንተ መምጣታችን ፍሬቢስ እንዳልነበረ እናንተው እራሳችሁ ታውቃላችሁ፣
2ነገር ግን እንደምታውቁት ቀደም ሲል በፊልጵስዩስ መከራና እንግልት ደረሰብን። በብዙ ተቃውሞ መካከል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ለመንገር አምላካችን ድፍረት ሰጥቶናል።
3የምንመክራችሁ ምክር ከስሕተት ወይም ከእርኩሰት ወይም ከማታለል የመነጨ አይደለም፣
4ነገር ግን ወንጌልን በአደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር ታማኞች አድርጎ እንደቆጠረን እንዲሁ ሰውን ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እርሱን ደስ ለማሰኘት እንናገራለን።
5እናንተው እንደምታውቁት መቼም ቢሆን የሽንገላን ቃል አልተጠቀምንም፣ ገንዘባችሁን በመመኘት እንዳልሆነም እግዚአብሔር ምስክር ነው፣
6የክርስቶስ ሐዋርያት እንደመሆናችን ልንጠቀምባችሁ መብት ቢኖረንም እንኳን ከእናንተ ወይም ከሌሎች ክብርን ከማንም ሰው አልፈለግንም።
7ይልቁንም እናት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን።
8ለእናንተ ካለን ፍቅር የተነሳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የራሳችንን ሕይወት እንኳን ጨምረን ብንካፈላችሁ ደስ ይለን ነበር፣ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችኋልና።
9ወንድሞች ሆይ! የእግዚአብሔርን ወንጌል በሰበክንላችሁ ጊዜ በማናችሁም ላይ ሸክም ላለመሆን ቀንና ሌሊት እንደሠራን ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሳላችሁ።
10በእናንተ በምታምኑት መካከል እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅና ነቀፋ በሌለበት ኑሮ ራሳችንን እንዳቀረብንላችሁ እግዚአብሔርና እናንተም ጭምር ምስክሮች ናችሁ፣
11እናንተው እንደምታውቁት አባት ለራሱ ልጆች እንደሚያደርገው እያንዳንዳችሁን መከርናችሁ፣ አበረታታናችሁና
12መሰከርንላችሁ፣ይኸውም ወደ ራሱ መንግሥትና ክብር ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ ነው።
13በዚህ ምክንያት እኛ ደግሞ ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፣ የመልዕክቱን ቃል፣ የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን፣ ነገር ግን እውነት እንደሆነ፣ በእናንተ በምታምኑት ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበላችሁት።
14እናንተም ወንድሞች ሆይ፣ በይሁዳ የሚኖሩ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑትን የእግዚአብሔር አብያተክርስቲያናት የምትመስሉ ሆናችኋል፣ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደደረሰባቸው እናንተ ደግሞ ከገዛ ራሳችሁ ሕዝብ ያንኑ መከራ ተቀብላችኋልና፣
15አይሁድ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፣ እኛንም አሳደዱን፣ እነርሱ እግዚአብሔርን ደስ አያሰኙትም፥ ሰውን ሁሉ ይቃወማሉ።
16ዘወትር ኀጢአታቸውን ለማብዛትም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ይከለክሉናል። ቁጣው በላያቸው ላይ መጥቶባቸዋል።
17ወንድሞች ሆይ፣ እኛ ለጥቂት ጊዜ በልባችን ሳይሆን በአካል ተለይተናችሁ ነበር፣ በመሆኑም በነበረን ታላቅ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት የተቻለንን ያህል ጥረት አድርገናል፣
18ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፣ እኔ ጳውሎስም ከአንድም ሁለት ጊዜ ሞከርኩኝ፣ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየን።
19ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም የመክበራችን አክሊል እንደሌሎቹ ሁሉ እናንተ አይደላችሁምን?
20ምክንያቱም እናንተ ክብራችንና ደስታችን ናችሁ።