መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከብንያም ወገን ጽኑ ኃያል የሆነ አንድ ሰው ነበር። ስሙ ቂስ ሲሆን እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ ነበር።
2እርሱም ሳኦል የሚባል መልከ መልካም ወጣት ልጅ ነበረው። ከእርሱ የሚበልጥ መልከ መልካም ሰው በእስራኤል ሕዝብ መካከል አልነበረም። ከሕዝቡ ሁሉ ይልቅ ቁመቱ ረጅም ነበር።
3የሳኦል አባት የቂስ ሴት አህዮች ጠፍተው ነበር። ስለዚህ ቂስ ልጁን ሳኦልን፥ “ከአገልጋዮቻችን አንዱን ውሰድ፤ ተነሥናም አህዮቹን ፈልግ” አለው።
4ስለዚህ ሳኦል በኮረብታማው በኤፍሬም አገር በኩል አልፎ ወደ ሻሊሻ ምድር ሄደ፥ ነገር ግን አላገኟቸውም። ከዚያም በሻዕሊም ምድር በኩል አለፉ፥ ነገር ግን በዚያ አልነበሩም። ከዚያም በብንያማውያን ምድር በኩል አለፉ፥ ነገር ግን አላገኟቸውም።
5ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜ፥ ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን አገልጋዩን፥ "ና እንመለስ፥ አለበለዚያ አባቴ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ይጀምራል" አለው።
6ነገር ግን አገልጋዩ እንዲህ አለው፥ “ስማኝ፥ በዚህ ከተማ ውስጥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ። እርሱም የተከበረ ሰው ነው፤ የሚናገረው ነገር ሁሉ ይፈጸማል። ወደዚያ እንሂድ፤ በየትኛው አቅጣጫ መሄድ እንዳለብን ሊነግረን ይችል ይሆናል"።
7ከዚያም ሳኦል አገልጋዩን፥ "ታዲያ ወደ እርሱ የምንሄድ ከሆነ ለዚያ ሰው ምን ልንሰጠው እንችላለን? እንጀራው ከከረጢታችን አልቋል፥ ለእግዚአብሔር ሰው የምናቀርበው ምንም ስጦታ የለንም። ምን አለን?"አለው።
8አገልጋዩም ለሳኦል፥ "ይኸውና፥ የሰቅል ጥሬ ብር አንድ አራተኛው አለኝ፥ በየትኛው አቅጣጫ መሄድ እንዳለብን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ" ሲል መለሰለት።
9(ቀደም ሲል በእስራኤል ውስጥ፥ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመጠየቅ በሚሄድበት ጊዜ፥ "ኑ፥ ወደ ባለ ራዕዩ እንሂድ" ይል ነበር። የዛሬው ነቢይ ቀደም ሲል ባለ ራዕይ ተብሎ ይጠራ
10ነበር።)ከዚያም ሳኦል አገልጋዩን፥”መልካም ብለሃል። ና፥ እንሂድ“ አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወደነበረበት ከተማ ሄዱ።
11ኮረብታው ላይ ወዳለው ከተማ በመውጣት ላይ እያሉ ወጣት ሴቶች ውሃ ለመቅዳት ሲወጡ አገኟቸው፤ ሳኦልና አገልጋዩም፥”ባለ ራዕዩ በዚህ አለ? “ በማለት ጠየቋቸው።
12እነርሱም እንዲህ በማለት መለሱላቸው፥ "አዎን፤ ተመልከቱ፥ እንዲያውም ከፊታችሁ እየቀደመ ነው። ዛሬ ሕዝቡ በኮረብታው ራስ ላይ ስለሚሠዉ ወደ ከተማው ይመጣልና ፍጠኑ።
13ወደ ከተማው እንደገባችሁ ለመብላት ወደ ኮረብታው ራስ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን የሚባርከው እርሱ ስለሆነ፥ እርሱ ከመምጣቱ በፊት ሕዝቡ አይበሉም፤ ከዚያ በኋላም የተጋበዙት ይበላሉ። ወዲያውኑ ታገኙታላችሁና አሁን ወደ ላይ ውጡ።”
14ስለዚህ ወደ ላይ ወደ ከተማው ወጡ። ወደ ከተማይቱ በመግባት ላይ እያሉም ሳሙኤል ወደ ኮረብታው ራስ ለመውጣት በእነርሱ አቅጣጫ ሲመጣ አዩት።
15ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፥
16“ነገ በዚህ ሰዓት ከብንያም ምድር አንድ ሰው እልክልሃለሁ፥ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መስፍን እንዲሆን ትቀባዋለህ። እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናቸዋል። እርዳታ በመፈለግ መጮኻቸው ወደ እኔ ደርሷልና ሕዝቤን በርኅራኄ ተመልክቻለሁ።”
17ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፥”ስለ እርሱ የነገርኩህ ሰው ይህ ነው! ሕዝቤን የሚገዛው ሰው እርሱ ነው።“
18ከዚያም ሳኦል በበሩ አጠገብ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፥”የባለ ራዕዩ ቤት የት እንደሆነ ንገረኝ“ አለው።
19ሳሙኤልም ለሳኦል እንዲህ በማለት መለሰለት፥”ባለ ራዕዩ እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት ቀድማችሁ ወደ ኮረብታው ራስ ውጡ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር ትበላላችሁና። ነገ ጠዋት በአዕምሮህ ያለውን ነገር ሁሉ እነግርህና አሰናብትሃለሁ።
20ከሦስት ቀን በፊት ጠፍተው የነበሩት አህዮች ተገኝተዋልና ስለ እነርሱ አታስብ። የእስራኤል ሁሉ ምኞት የተቀመጠው በማን ላይ ነው? በአንተና በአባትህ ቤት ሁሉ ላይ አይደለም? “
21ሳኦልም፥ "ከእስራኤል ነገዶች ትንሹ የሆነው ብንያማዊ አይደለሁም? ጎሳዬስ ከብንያም ነገድ ጎሳዎች ሁሉ የመጨረሻው አይደለም? ታዲያ እንዲህ ባለ ሁኔታ ለምን ትናገረኛለህ?"ሲል መለሰለት።
22ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አስገብቶ ሠላሳ ከሚያህሉ ከተጋበዙት ሰዎች ከፍ ባለው ስፍራ ላይ አስቀመጣቸው።
23ሳሙኤልም ወጥ ሠሪውን፥ "'ለብቻ አስቀምጠው' ብዬ የሰጠሁህን ድርሻ አምጣው" አለው።
24ወጥ ሠሪውም በመሥዋዕቱ ጊዜ ያነሣውን ጭኑንና ከእርሱ ጋር ያለውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ከዚያም ሳሙኤል፥ "የተቀመጠልህን ተመልከት! ለአንተ እስከተወሰነው ሰዓት ድረስ የቆየልህ ነውና ብላው። አሁን 'ሕዝቡን ጋብዣለሁ' ማለት ትችላለህ" አለው። ስለዚህ በዚያን ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ።
25ከኮረብታው ራስ ወደ ከተማው በወረዱ ጊዜ፥ በቤቱ የጣሪያ ወለል ላይ ሳሙኤል ከሳኦል ጋር ተነጋገረ።
26ከዚያም በነጋ ጊዜ ሳሙኤል በጣሪያው ወለል ላይ ሳኦልን ተጣርቶ፥ "መንገድህን እንድትሄድ አሰናብትህ ዘንድ ተነሥ" አለው። ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤል ሁለቱም ወደ ጎዳናው ሄዱ።
27ወደ ከተማው ዳርቻ በመሄድ ላይ እያሉ፥ ሳሙኤል ሳኦልን፥ "አገልጋዩ ከፊታችን ቀድሞ እንዲሄድ ንገረው፥ (እርሱም ቀድሞ ሄደ) አንተ ግን የእግዚአብሔርን መልዕክት እንዳስታውቅህ እዚህ ጥቂት መቆየት አለብህ" አለው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።