1ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አድርጎ ሾማቸው።
2የመጀመሪያ ልጁ ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛው ስም አብያ ነበር። እነርሱም በቤርሳቤህ ፈራጆች ነበሩ።
3ነገር ግን ልጆቹ ነውረኛ ጥቅም ፈላጊዎች ሆኑ እንጂ በእርሱ መንገድ አልሄዱም። ጉቦ እየተቀበሉ ፍትሕን አዛቡ።
4ከዚያም የእስራኤል ሽማግሌዎች በአንድነት ተሰብስበው በራማ ወደሚኖረው ወደ ሳሙኤል መጡ።
5እነርሱም፥ "ተመልከት፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም። እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ እንዲፈርድልን ንጉሥ አንግሥልን" አሉት።
6ነገር ግን፥ “እንዲፈርድልን ንጉሥ ስጠን” ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን ቅር አሰኘው። ስለዚህ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
7እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፥ “በላያቸው ላይ ንጉሥ እንዳልሆን የተቃወሙት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ታዘዝ።
8ከግብፅ ካወጣዃቸው ጊዜ ጀምሮ እኔን ትተው ሌሎች አማልክቶችን በማምለክ ሲያደርጉት የነበረውን ያንኑ አሁን እያደረጉ ነው፤ በአንተም ላይ የሚያደርጉት እንደዚሁ ነው።
9አሁንም የሚሉህን ስማቸው፤ ነገር ግን በላያቸው የሚገዛው ንጉሥ የሚያደርግባቸውን እንዲያውቁ አጥብቀህ አስጠንቅቃቸው"።
10ስለዚህ ሳሙኤል ንጉሥ ለጠየቀው ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ነገራቸው።
11እርሱም እንዲህ አላቸው፥ "ንጉሡ በላያችሁ ላይ የሚገዛው እንዲህ ነው። ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ፈረሰኞች እንዲሆኑና በሠረገላዎቹ ፊት እንዲሮጡ በሠረገላዎቹ ላይ ይሾማቸዋል።
12እርሱም ለራሱ ሻለቃዎችንና ሃምሳ አለቃዎችን ይሾማል። አንዳንዶቹ መሬቱን እንዲያርሱ፥ ሌሎቹም እህሉን እንዲያጭዱ፥ አንዳንዶቹ የጦር መሳሪያዎችንና ሌሎቹም የሠረገላ ዕቃዎችን እንዲሠሩለት ያደርጋቸዋል።
13ሴቶች ልጆቻችሁን ደግሞ ሽቶ ቀማሚዎች፥ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች እንዲሆኑ ይወስዳቸዋል።
14በጣም ምርጥ የሆነውን መሬታችሁን፥ የወይን ቦታችሁንና የወይራ ዛፋችሁን ወስዶ ለአገልጋዮቹ ይሰጣቸዋል።
15ከእህላችሁና ከወይናችሁ አንድ ዐሥረኛውን ወስዶ ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ ይሰጣቸዋል።
16ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁን፥ ከወጣት ልጆቻችሁና ከአህዮቻችሁ የተመረጡትን ይወስዳል፤ ሁሉንም ለእርሱ እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል።
17ከበግና ከፍየል መንጋዎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ይወስዳል፥ እናንተም አገልጋዮቹ ትሆናላችሁ።
18በዚያም ቀን ለራሳችሁ ስለመረጣችሁት ንጉሥ ታለቅሳላችሁ፤ ነገር ግን በዚያን ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም”።
19ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን ለመስማት እምቢ አሉ፤
20ሳሙኤልንም፥ “አይሆንም፥ ንጉሣችን እንዲፈርድልን፥ በፊታችን እንዲሄድና ጦርነቶቻችንን እንዲዋጋልን፥ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ለእኛም ንጉሥ ሊሆንልን ይገባል” አሉት።
21ሳሙኤል የሕዝቡን ቃል ሁሉ በሰማ ጊዜ እርሱም በእግዚአብሔር ጆሮ ደግሞ ተናገረው።
22እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “ቃላቸውን ታዘዝና ንጉሥ አድርግላቸው” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፥ “እያንዳንዱ ወደገዛ ከተማው ይሂድ” አላቸው።