1ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ጠርሙስ ወስዶ በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም። እርሱም እንዲህ አለው፥ "በርስቱ ላይ ገዢ እንድትሆን እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤
2ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፥ የብንያም ወሰን በሆነው በጼልጻህ፥ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፥ 'ስትፈልጋቸው የነበሩት አህዮች ተገኝተዋል። አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፥ "ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?" በማለት ተጨንቋል“ ይሉሃል።
3ከዚያ አልፈህ ትሄድና በታቦር ወደሚገኘው ወደ በሉጥ ዛፍ ትመጣለህ። ወደ ቤቴል፥ ወደ እግዚአብሔር የሚሄዱ አንደኛው ሦስት የፍየል ጠቦቶች ይዞ፥ ሌላኛው ሦስት ዳቦ ተሸክሞ፥ ሌላኛው ደግሞ ወይን ጠጅ የተሞላ አንድ አቁማዳ ተሸክሞ ሦስት ሰዎች ይገናኙሃል።
4ሰላምታ ከሰጡህ በኋላ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላቸዋለህ።
5ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤም የጦር ሠፈር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ። ወደ ከተማው በምትደርስበት ጊዜ፥ አንድ የነቢያት ቡድን በፊታቸው መሰንቆ፥ ከበሮ፥ እምቢልታና በገና ይዘው ከተራራው ሲወርዱ ትገናኛቸዋለህ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።
6የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ይመጣብሃል፥ አንተም ከእነርሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰው ሆነህም ትለወጣለህ።
7እነዚህ ምልክቶች በሚፈጸሙልህ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ ያገኘውን ሁሉ አድርግ።
8ቀድመኸኝ ወደ ጌልገላ ውረድ። ከዚያም የሚቃጠለውን መባ ለማቅረብና የሰላሙን መባ ለመሠዋት ወደ አንተ እወርዳለሁ። ወደ አንተ እስክመጣና ልታደርገው የሚገባህን እስከማሳይህ ድረስ ሰባት ቀን ቆይ።”
9ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን ባዞረ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ሰጠው። እነዚህ ምልክቶች ሁሉ በዚያው ቀን ተፈጸሙ።
10እነርሱም ወደ ኮረብታው በመጡ ጊዜ፥ የነቢያት ቡድን ተገናኙት፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል መጣበት፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ።
11ቀድሞ ያውቁት የነበሩት ሁሉ እርሱም ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፥ እርስ በእርሳቸው፥ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? አሁን ሳኦል ከነቢያት አንዱ መሆኑ ነው?” ተባባሉ።
12በዚያው ስፍራ የነበረ አንድ ሰው፥ “አባታቸው ማነው?” ሲል መለሰ። በዚህ ምክንያት፥ “ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ነው?” የሚል ምሳሌአዊ አባባል የተለመደ ሆነ።
13ትንቢት መናገሩን በጨረሰ ጊዜ ወደ ተራራው ራስ መጣ።
14ከዚያም የሳኦል አጎት፥ እርሱንና አገልጋዩን፥ “የት ነበር የሄዳችሁት?” አላቸው። እርሱም፥ “አህዮቹን ለመፈለግ ነበር፤ ልናገኛቸው እንዳልቻልን ባየን ጊዜ ወደ ሳሙኤል ሄድን” ብሎ መለሰለት።
15የሳኦልም አጎት፥ “ሳሙኤል የነገረህን እባክህ ንገረኝ" አለው።
16ሳኦልም አጎቱን፥ "አህዮቹ መገኘታቸውን በግልጽ ነገረን" ብሎ መለሰለት። ሳሙኤል ነግሮት የነበረውን የንግሥና ጉዳይ ግን አልነገረውም።
17ሳሙኤል ሕዝቡን በአንድነት በእግዚአብሔር ፊት ወደ ምጽጳ ጠራቸው።
18እርሱም የእስራኤልን ሕዝብ እንዲህ አላቸው፥”የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህንን ነው፥ 'እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁት፥ ከግብፃውያን እጅና ካስጨነቋችሁ መንግሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ'።
19ነገር ግን ዛሬ እናንተ ከመከራና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ተቃውማችኋል፤ እርሱንም፥ 'በላያችን ላይ ንጉሥ አንግሥልን' ብላችሁታል። አሁን በየነገዳችሁና በየጎሣችሁ ራሳችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ"።
20ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ አቀረበ፥ የብንያም ነገድም ተመረጠ።
21ከዚያም የብንያምን ነገድ በየጎሣቸው አቀረበ፤ የማጥሪ ጎሣም ተመረጠ፤ የቂስ ልጅ ሳኦልም ተመረጠ። ነገር ግን በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙት አልቻሉም።
22ከዚያም ሕዝቡ”ገና የሚመጣ ሌላ ሰው አለ? “ በማለት እግዚአብሔርን ተጨማሪ ጥያቄዎች ለመጠየቅ ፈለጉ። እግዚአብሔርም፥”ራሱን በዕቃዎቹ መካከል ደብቋል" በማለት መለሰላቸው።
23ከዚያም ሮጠው ሄዱና ሳኦልን ከዚያ አመጡት። በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜ፥ ከሕዝቡ ሁሉ ይልቅ ቁመቱ ረጅም ነበር።
24ሳሙኤልም ሕዝቡን፥ "እግዚአብሔር የመረጠውን ይህንን ሰው ታዩታላችሁ? በሕዝቡ ሁሉ መካከል እንደ እርሱ ያለ የለም! “ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ፥”ንጉሥ ለዘላለም ይኑር! “ በማለት ጮኹ።
25ከዚያም ሳሙኤል የንግሥናን ደንብና ልማዶች ለሕዝቡ ነገራቸው፥ በመጽሐፍ ጽፎም በእግዚአብሔር ፊት አስቀመጣቸው። ከዚያም ሳሙኤል እያንዳንዱ ወደ ገዛ መኖሪያው እንዲሄድ ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ።
26ሳኦልም ደግሞ በጊብዓ ወደሚገኘው መኖሪያው ሄደ፥ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካቸው አንዳንድ ኃያላን ሰዎችም ከእርሱ ጋር ሄዱ።
27አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ግን፥”ይህ ሰው ሊያድነን እንዴት ይችላል? “ አሉ። እነዚህ ሰዎች ሳኦልን ናቁት፥ ምንም ዓይነት ስጦታዎችንም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።