መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የቂርያትይዓሪም ሰዎች መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ፥ በኮረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አስገቡት። የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ለዚህ አገልግሎት ለዩት።
2ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ብዙ ዓመት አለፈው፥ ሃያ ዓመትም ሆነው። የእስራኤል ቤት ሁሉ አዘኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስም ፈለጉ።
3ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ በሙሉ እንዲህ አላቸው፥ "በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ እንግዶቹን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ልባችሁን ወደ እግዚአብሔር መልሱ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩት፥ ያን ጊዜ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናችኋል"።
4ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ በኣልንና አስታሮትን አስወገዱ፥ እግዚአብሔርን ብቻም አመለኩ።
5ከዚያም ሳሙኤል፥ "እስራኤልን በሙሉ ምጽጳ ላይ ሰብስቡ፥ እኔም ስለ እናንተ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ“ አላቸው።
6እነርሱም በምጽጳ ተሰበሰቡ፥ ውሃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ። በዚያም ቀን ጾሙ፥”በእግዚአብሔር ላይም ኃጢአትን አድርገናል“ አሉ። ሳሙኤል በእስራኤል ሕዝብ ላይ የፈረደውና ሕዝቡን የመራው በዚያ ነበር።
7የእስራኤል ሕዝብ በምጽጳ መሰብሰባቸውን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፥ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች እስራኤልን ለማጥቃት መጡ። የእስራኤል ሰዎች ይህንን በሰሙ ጊዜ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ።
8ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ሳሙኤልን፥”ከፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲያድነን፥ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር መጣራትህን አታቁም“ አሉት።
9ሳሙኤል የሚጠባ ግልገል ወስዶ ለእግዚአብሔር ሙሉውን የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ ሠዋው። ከዚያም ሳሙኤል ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም መለሰለት።
10ሳሙኤል የሚቃጠለውን መስዋዕት በማቅረብ ላይ እያለ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለማጥቃት ቀረቡ። ነገር ግን በዚያን ቀን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ በታላቅ ድምፅ አንጎደጎደባቸው፥ አሸበራቸውም፥ በእስራኤልም ፊት ተሸንፈው ሸሹ።
11የእስራኤል ሰዎችም ከምጽጳ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን አሳደዱ፥ ከቤትካር በታች እስካለው ቦታ ድረስ ተከትለው ገደሏቸው።
12ከዚያም ሳሙኤል አንድ ድንጋይ አንሥቶ በምጽጳና በሼን መካከል አቆመው።”እስካሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል“ በማለት አቤንኤዘር ብሎ ጠራው።
13ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፥ የእስራኤልን ድንበርም አልፈው አልገቡም። በሳሙኤል የሕይወት ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ከብዳ ነበር።
14ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል የወሰዷቸው ከአቃሮን እስከ ጌት ያሉ መንደሮች ለእስራኤል ተመለሱላቸው፤ እስራኤላውያን ድንበሮቻቸውን ከፍልስጥኤማውያን አስመለሱ። በዚያን ጊዜ በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከል ሰላም ነበረ።
15ሳሙኤል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእስራኤል ላይ ፈረደ።
16በየዓመቱ ወደ ቤቴል፥ ወደ ጌልገላና ወደ ምጽጳ ይዘዋወር ነበር። በእነዚህ ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤላውያን መካከል ባሉ አለመግባባቶች ላይ ይፈርድ ነበር።
17ከዚያም መኖሪያው በዚያ ነበርና ወደ ራማ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ደግሞ በእስራኤላውያን አለመግባባት ላይ ይፈርድ ነበር። በዚያም ደግሞ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።