መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ከተቀመጠ ሰባት ወር ሆነው።
2ከዚያም የፍልስጥኤም ሰዎች ካህናትንና ጠንቋዮችን ጠርተው፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ምን እናድርገው? ወደ አገሩ እንዴት አድርገን መመለስ እንዳለብን ንገሩን” አሉአቸው።
3ካህናቱና ጠንቋዮቹም፥ "የእስራኤልን አምላክ ታቦት መልሳችሁ የምትልኩ ከሆነ ያለስጦታ አትላኩት፤ በተቻለ መጠን የበደል መስዋዕትም ላኩለት። ከዚያም ትፈወሳላችሁ፥ እናንተም እስካሁን ድረስ እጁን ከላያችሁ ላይ ያላነሣው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ"።
4ሕዝቡም፥ “የምንመልሰው የበደል መስዋዕት ምን መሆን አለበት?”አሏቸው። እነርሱም እንዲህ በማለት መለሱላቸው፥ "አምስት የወርቅ እባጮችንና አምስት የወርቅ አይጦችን፥ በቁጥር አምስት መሆኑም የፍልስጥኤማውያንን ገዢዎች ቁጥር የሚወክል ነው። እናንተንና ገዢዎቻችሁን የመታው ተመሳሳይ መቅሰፍት ነውና።
5ስለዚህ ምድራችንን ባጠፋው በእባጮቻችሁና በአይጦቻችሁ አምሳል ማድረግ አለባችሁ፥ ለእስራኤል አምላክም ክብርን ስጡ። ምናልባት እጁን ከእናንተ፥ ከአማልክቶቻችሁና ከምድሪቱ ላይ ያነሣ ይሆናል።
6ግብፃውያንና ፈርዖን ልባቸውን እንዳደነደኑ ለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ? ያን ጊዜ ነበር የእስራኤል አምላክ ክፉን ያደረገባቸው፤ ታዲያ ግብፃውያኑ ሕዝቡን አልለቀቋቸውም?እነርሱስ ከዚያ አልወጡም?
7እንግዲህ አዲስ ሠረገላና እስካሁን ቀንበር ያልተጫነባቸውን ሁለት የሚያጠቡ ላሞች አዘጋጁ። ላሞቹን በሠረገላው ጥመዷቸው፥ እምቦሳዎቻቸውን ግን ከእነርሱ ለይታችሁ በቤት አስቀሩአቸው።
8ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩት። የበደል መስዋዕት አድርጋችሁ የምትመልሱለትን የወርቁን አምሳያዎች በሳጥን ውስጥ አድርጋችሁ በአንደኛው ጎኑ አስቀምጡ። ከዚያም ልቀቁትና በራሱ መንገድ እንዲሄድ ተዉት።
9ከዚያም ተመልከቱ፥ ወደ ራሱ ምድር፥ ወደ ቤት ሳሚስ በመንገዱ ከሄደ፥ ይህንን ታላቅ ጥፋት ያመጣው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን፥ ይህ በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን"።
10ሰዎቹም እንደተነገራቸው አደረጉ፤ ሁለት የሚያጠቡ ላሞችን ወሰዱና በሠረገላው ጠመዷቸው፥ እምቦሳዎቻቸውንም ከቤት እንዳይወጡ አደረጉ።
11የወርቁን አይጥና የእባጮቻቸው ምሳሌ የሆነውን ከያዘው ሳጥን ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት በሠረገላው ላይ አደረጉት።
12ላሞቹም በቤት ሳሚስ አቅጣጫ ቀጥ ብለው ሄዱ። እነርሱም በዚያው ጎዳና፥ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይሉ ቁልቁል ሄዱ። የፍልስጥኤማውያን ገዢዎችም እስከ ቤት ሳሚስ ዳርቻ ድረስ ከበስተኋላቸው ተከተሏቸው።
13በዚህ ጊዜ የቤት ሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴአቸውን በማጨድ ላይ ነበሩ። ቀና ብለው ባዩ ጊዜ ታቦቱን ተመለከቱ፥ ደስም አላቸው።
14ሠረገላው የቤት ሳሚስ ሰው ወደሆነው ወደ ኢያሱ እርሻ መጥቶ በዚያ ቆመ። በዚያም ትልቅ ቋጥኝ ነበር፥ የሠረገላውን እንጨት በመፍለጥ ላሞቹን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።
15ሌዋውያኑ የእግዚአብሔርን ታቦትና አብሮት የነበረውን፥ የወርቁ ምስሎች የነበሩበትን ሳጥን፥ ከሠረገላው አውርደው በትልቁ ቋጥኝ ላይ አስቀመጡት። በዚያው ቀን የቤት ሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀርቡ፥ መሥዋዕቶችንም ሠዉ።
16አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ይህንን ባዩ ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አቃሮን ተመለሱ።
17የፍልስጥኤም ሰዎች ለእግዚአብሔር የበደል መስዋዕት አድርገው የመለሷቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዱ ስለ አሽዶድ፥ አንዱ ስለ ጋዛ፥ አንዱ ስለ አስቀሎና፥ አንዱ ስለ ጌት እና አንዱ ስለ አቃሮን ነበር።
18የወርቁ አይጥ አምስቱ ገዢዎች ከሚገዟቸው የተመሸጉ የፍልስጥኤማውያን ከተሞችና መንደሮች ቁጥር ሁሉ ጋር ቁጥሩ ተመሳሳይ ነበር። የእግዚአብሔርን ታቦት ያስቀመጡበት ያ ታላቅ ቋጥኝ በቤት ሳሚስ በኢያሱ እርሻ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ምስክር ሆኖ ይኖራል።
19ወደ ታቦቱ ውስጥ ተመልክተዋልና እግዚአብሔር ከቤት ሳሚስ ሰዎች ጥቂቶቹን መታቸው። እርሱም ሰባ ሰዎችን ገደለ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ክፉኛ ስለመታቸው ሕዝቡ አለቀሱ።
20የቤት ሳሚስ ሰዎችም፥ “በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚችል ማነው? ከእኛስ ወደ ማን ይሄዳል?” አሉ።
21በቂርያትይዓሪም ወደሚኖሩት መልዕክተኞች ልከው፥ “ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፤ ወደዚህ ውረዱና ውሰዱት” አሏቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።