1የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤላውያን ሁሉ መጣ። በዚህ ወቅት እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ለመዋጋት ሄዱ። የጦር ሰፈራቸውንም በአቤንኤዘር አደረጉ፥ ፍልስጥኤማውያንም የጦር ሰፈራቸውን በአፌቅ አደረጉ።
2ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ተሰለፉ። ውጊያው በተፋፋመ ጊዜ እስራኤላውያን አራት ሺህ ሰዎቻቸው በውጊያው ሜዳ በመገደላቸው በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ።
3ሕዝቡ ወደ ጦር ሰፈሩ በመጣ ጊዜ፥ የእስራኤል ሽማግሌዎች፥ "እግዚአብሔር ዛሬ በፍልስጥኤማውያን ፊት እንድንሸነፍ ያደርገን ለምንድነው? ከእኛ ጋር እንዲሆንና ከጠላቶቻችን ኃይል እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ እናምጣው" አሉ።
4ስለዚህ ሕዝቡ ወደ ሴሎ ሰዎችን ላኩ። ከዚያ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊቱን ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ። ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ጦር ሰፈሩ በመጣ ጊዜ፥ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ በታላቅ ዕልልታ ጮኹ፥ ምድሪቱም አስተጋባች።
6ፍልስጥኤማውያን የዕልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ “ይህ በዕብራውያኑ የጦር ሰፈር የሚሰማው የዕልልታ ድምፅ ምን ማለት ይሆን? አሉ። ከዚያም የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ጦር ሰፈሩ እንደ መጣ ተገነዘቡ።
7ፍልስጥኤማውያኑ ፈሩ፤ እነርሱም፥”እግዚአብሔር ወደ ጦር ሰፈሩ መጥቷል" አሉ።
8እነርሱም፥ "ወዮልን! እንደዚህ ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልሆነም! ወዮልን! ከዚህ ኃያል አምላክ ክንድ ማን ያድነናል? ይህ በምድረ በዳ ግብፃውያንን በልዩ ልዩ ዓይነት መቅሠፍት የመታቸው አምላክ ነው።
9እናንተ ፍልስጥኤማውያን በርቱ፥ ወንድነታችሁንም አሳዩ፥ ካልሆነ እነርሱ ባሪያዎቻችሁ እንደነበሩ ባሪያዎቻቸው ትሆናላችሁ። ወንድነታችሁ ይታይ፥ ተዋጉም" አሏቸው።
10ፍልስጥኤማውያኑ ተዋጉ፥ እስራኤላውያንም ተሸነፉ። እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሸሸ፥ የተገደሉትም እጅግ ብዙ ነበሩ፤ ከእስራኤል ሠላሳ ሺህ እግረኛ ወታደር ወደቀ።
11የእግዚአብሔር ታቦት ተወሰደ፥ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ሞቱ።
12በዚያው ቀን አንድ ብንያማዊ ከውጊያው መስመር ወደ ሴሎ በሩጫ መጣ፥ በደረሰ ጊዜ ልብሱን ቀድዶና በራሱ ላይ አፈር ነስንሶ ነበር።
13እርሱ በደረሰ ጊዜ፥ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት በመስጋት ልቡ ታውኮበት ስለነበረ በመንገዱ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። ሰውየው ወደ ከተማ ገብቶ ወሬውን በነገራቸው ጊዜ፥ ከተማው በሙሉ አለቀሱ።
14ዔሊ የልቅሶውን ድምፅ በሰማ ጊዜ፥ “የዚህ ሁካታ ትርጉሙ ምንድነው?” አለ። ሰውየው ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው።
15በዚህ ጊዜ ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ ዓይኖቹ አጥርተው አያዩም ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር።
16ሰውየውም ዔሊን፥ “ከውጊያው መስመር የመጣሁት እኔ ነኝ። ዛሬ ከውጊያው ሸሽቼ መጣሁ” አለው። ዔሊም፥ “ልጄ ሆይ፥ ነገሩ እንዴት እየሆነ ነው?” አለው።
17ወሬውን ያመጣው ያ ሰው መልሶ፥ “እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። ደግሞም በሕዝቡ መካከል ታላቅ ዕልቂት ሆኗል። ሁለቱ ወንዶች ልጆችህ፥ አፍኒን እና ፊንሐስ ሞተዋል፥ የእግዚአብሔር ታቦትም ተወስዷል” አለው።
18እርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ጠቅሶ በተናገረ ጊዜ፥ ዔሊ በመግቢያው በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወደ ኋላው ወደቀ። ስላረጀና ውፍረት ስለነበረው አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤላውያን ላይ ለአርባ ዓመታት ፈርዶ ነበር።
19በዚህ ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት አርግዛ የመውለጃ ሰዓቷ ደርሶ ነበር። የእግዚአብሔር ታቦት መማረኩን፥ ዐማቷና ባሏ መሞታቸውን በሰማች ጊዜ ተንበርክካ ወለደች፥ ነገር ግን ምጡ አስጨነቃት።
20ለመሞት በምታጣጥርበት ጊዜ ያዋልዷት የነበሩ ሴቶች፥ "ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ“ አሏት። እርሷ ግን አልመለሰችላቸውም ወይም የነገሯትን በልቧ አላኖረችውም።
21እርሷም የእግዚአብሔር ታቦት ስለተማረከና ስለ ዐማቷና ስለ ባልዋ "ክብር ከእስራኤል ተለየ!" ስትል ልጁን ኤካቦድ ብላ ጠራችው።
22እርሷም፥”የእግዚአብሔር ታቦት ስለተማረከ ክብር ከእስራኤል ተለየ!" አለች።