1ትንሹ ልጅ ሳሙኤል በዔሊ ሥር ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
2በእነዚያ ቀናት የእግዚአብሔር ቃል እምብዛም አይገኝም ነበር፤ ትንቢታዊ ራዕይም አይዘወተርም ነበር። በዚያን ጊዜ፥ ዔሊ ዐይኖቹ ከመፍዘዛቸው የተነሣ አጥርቶ ማየት ባቃተው ጊዜ፥ በአልጋው ላይ ተኝቶ እያለ፥
3የእግዚአብሔር መብራት ገና አልጠፋም ነበር፥ ሳሙኤል የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተኝቶ ነበር።
4እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፥ እርሱም፥ “አቤት!” አለው።
5ሳሙኤል ወደ ዔሊ ሮጠና፥ “ጠርተኸኛልና ይኸው መጥቻለሁ” አለው፤ ዔሊም፥ “እኔ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ሄደና ተኛ።
6እግዚአብሔር እንደገና፥ “ሳሙኤል” ብሎ ተጣራ። ሳሙኤልም እንደገና ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፥ “ጠርተኸኛልና ይኸው መጥቻለሁ” አለው። ዔሊም፥ "ልጄ ሆይ፥ እኔ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ" ብሎ መለሰለት።
7ሳሙኤል እግዚአብሔርን ገና አላወቀም ነበር፥ ከእግዚአብሔር ምንም ዓይነት መልዕክት ገና አልተገለጠለትም ነበር።
8እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው። ሳሙኤልም እንደገና ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፥ “ጠርተኸኛልና ይኸው መጥቻለሁ” አለው። ከዚያም ልጁን እግዚአብሔር እንደ ጠራው ዔሊ አስተዋለ።
9ዔሊም ሳሙኤልን፥ "ሂድና ተመልሰህ ተኛ፤ ደግሞ ከጠራህም፥ 'እግዚአብሔር ሆይ፥ አገልጋይህ እየሰማህ ነውና ተናገር' ማለት አለብህ" አለው። ስለዚህ ሳሙኤል እንደገና ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ።
10እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፤ እንደ ቀድሞው ሁሉ፥ "ሳሙኤል፥ ሳሙኤል" ብሎ ጠራው። ከዚያም ሳሙኤል፥ "አገልጋይህ እየሰማህ ነውና ተናገር" አለው።
11እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፥ "ተመልከት፥ የሚሰማውን ሁሉ ጆሮውን ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።
12በዚያም ቀን፥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ስለ ቤቱ የተናገርኩትን ሁሉ በዔሊ ላይ አመጣበታለሁ።
13ልጆቹ በራሳቸው ላይ እርግማንን ስላመጡና እርሱም ስላልከለከላቸው፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርሱ ስለሚያውቀው ኃጢአት በቤቱ ላይ እንደምፈርድ ነግሬዋለሁ።
14በዚህ ምክንያት የቤቱ ኃጢአት በመሥዋዕት ወይም በመባ ይቅር እንዳይባል ለዔሊ ቤት ምያለሁ።"
15ሳሙኤል እስኪነጋ ተኛ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ። ሳሙኤል ግን ስላየው ራዕይ ለዔሊ ለመንገር ፈራ።
16ከዚያም ዔሊ ሳሙኤልን ጠርቶ፥ "ልጄ ሳሙኤል ሆይ" አለው። ሳሙኤልም፥ "አቤት!" ብሎ መለሰለት።
17እርሱም፥ "የነገረህ ቃል ምንድነው? እባክህ አትደብቀኝ። ከነገረህ ቃል ሁሉ አንዱን ብትደብቀኝ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብህ፤ ከዚያም የባሰውን ጨምሮ ያድርግብህ" አለው።
18ሳሙኤል ሁሉንም ነገር ነገረው፤ ከእርሱም ምንም አልደበቀም። ዔሊም፥ "እርሱ እግዚአብሔር ነው። መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ" አለ።
19ሳሙኤል አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር፥ ከትንቢታዊ ቃሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም አልነበረም።
20ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉት እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን መመረጡን ዐወቁ።
21እግዚአብሔር እንደገና በሴሎ ተገለጠ፥ እርሱም በቃሉ አማካይነት በሴሎ ራሱን ለሳሙኤል ገለጠለት።