መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 30

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንዲህም ሆነ፥ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ አማሌቃውያን በኔጌቭና በጺቅላግ ላይ ወረራ ፈጽመው ነበር። እነርሱም ጺቅላግን መቱ፥ አቃጠሏትም፥
2ሴቶችንና በውስጧ የነበረውን ትንሽና ትልቅ ሁሉ ማረኩ። ይዘዋቸው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንዱንም አልገደሉም።
3ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ከተማይቱ በመጡ ጊዜ ከተማይቱ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው ተወስደው ነበር።
4ከዚያም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ለማልቀስ ኃይል እስከማይኖራቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
5ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች፥ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር።
6የሕዝቡም ሁሉ መንፈስ፥ እያንዳንዱም ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ስላዘነ በድንጋይ ሊወግሩት ይነጋገሩ ስለነበር ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ራሱን አበረታ።
7ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፥ "ኤፉዱን ወደዚህ እንድታመጣልኝ እለምንሃለሁ" አለው። አብያታር ኤፉዱን ለዳዊት አመጣለት።
8ዳዊትም ምሪት ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር፥ "ይህንን ወራሪ ብከተል እደርስበታለሁ?" ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም፥ "ተከተላቸው፥ ያለጥርጥር ትደርስባቸዋለህ፥ ሁሉንም ነገር ታስመልሳለህ" ብሎ መለሰለት።
9ስለዚህ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፤ ከእነርሱ ወደ ኋላ የቀሩት ወደሚቆዩበት ወደ ባሦር ወንዝ መጡ።
10ነገር ግን ዳዊት ከአራት መቶ ሰዎች ጋር መከታተሉን ቀጠለ፤ ሁለት መቶዎቹ በጣም ስለ ደከሙ የባሦርን ወንዝ መሻገር አልቻሉምና ወደ ኋላ ቀሩ።
11እነርሱም በሜዳው ላይ አንድ ግብፃዊ አገኙና ወደ ዳዊት አመጡት፤ ምግብ ሰጡትና በላ፥ እንዲጠጣም ውሃ ሰጡት፤
12ደግሞም ከበለስ ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት። ለሦስት ቀንና ሌሊት ምንም ምግብ አልበላም፥ ውሃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ እንደገና ብርታት አገኘ።
13ዳዊትም፥ "አንተ የማን ነህ? ከየትስ ነው የመጣኸው?" አለው። እርሱም፥ "እኔ የአማሌቃዊ አገልጋይ፥ ግብፃዊ ወጣት ነኝ፤ ከሦስት ቀናት በፊት ታምሜ ስለነበር ጌታዬ ትቶኝ ሄደ።
14እኛም በከሊታውያን ኔጌቭ፥ የይሁዳ በሆነው ምድርና በካሌብ ኔጌቭ ላይ ወረራ ፈጸምን፥ ጺቅላግንም አቃጠልናት“ አለው።
15ዳዊትም፥”ወደዚህ ወራሪ አካል መርተህ ልታወርደኝ ትፈቅዳለህ? “ አለው። ግብፃዊውም፥”እንዳትገድለኝ ወይም በጌታዬ እጅ ላይ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ ወደ ወራሪው አካል መርቼ አወርድሃለሁ“ አለው።
16ግብፃዊው ዳዊትን እየመራው ወደ ታች ባወረደው ጊዜ፥ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያን ምድርና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ምርኮ ሁሉ የተነሣ እየበሉና እየጠጡ፥ እየጨፈሩም በምድሩ ሁሉ ተበትነው ነበር።
17ዳዊትም ደንገዝገዝ ሲል ጀምሮ እስከ ማግስቱ ምሽት ድረስ መታቸው። በግመሎች ተቀምጠው ከሸሹት ከአራት መቶ ወጣቶች በስተቀር አንድም ሰው አላመለጠም።
18ዳዊት አማሌቃውያን ወስደዋቸው የነበሩትን ሁሉ አስመለሰ፤ ሁለቱን ሚስቶቹንም አዳነ።
19ትንሽ ይሁን ትልቅ፥ ወንዶች ልጆች ይሁኑ ሴቶች ልጆች፥ ምርኮም ይሁን ወራሪዎቹ ለራሳቸው ከወሰዱት ማንኛውም ነገር አንዱም አልጠፋም። ዳዊት ሁሉን ነገር አስመለሰ።
20ዳዊትም ሰዎቹ ከሌሎች ከብቶች ፊት ይነዷቸው የነበሩትን የበጉን፥ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ። እነርሱም፥ "ይህ የዳዊት ምርኮ ነው" አሉ።
21ዳዊት ሊከተሉት እጅግ ደክሟቸው በባሦር ወንዝ አጠገብ እንዲቆዩ ወደተደረጉት ወደ ሁለት መቶዎቹ ሰዎች መጣ። እነዚህ ሰዎች ዳዊትንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ለመገናኘት ወጡ። ዳዊት ወደ እነዚህ ሰዎች በመጣ ጊዜ ሰላምታ ሰጣቸው።
22ከዚያም ከዳዊት ጋር ሄደው በነበሩት ሰዎች መካከል ክፉዎችና የማይረቡት ሁሉ፥”እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከመሄድ በስተቀር እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር ስላልሄዱ፥ ካስመለስነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም“ አሉ።
23ከዚያም ዳዊት፥”ወንድሞቼ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ ልታደርጉ አይገባም። እርሱ ጠበቀን፥ በእኛ ላይ የመጡትንም ወራሪዎች በእጃችን ላይ አሳልፎ ሰጠን።
24በዚህ ጉዳይ ማን ይሰማችኋል? ወደ ጦርነት የሄደው የየትኛውም ሰው ድርሻ ስንቅና ትጥቅ ከጠበቀ ከየትኛውም ሰው ድርሻ ጋር እኩል ይሆናል፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉ" አላቸው።
25ዳዊት ለእስራኤል ደንብና ሥርዓት ስላደረገው፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደዚሁ ሆነ።
26ዳዊት ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ፥ ከምርኮው ጥቂቱን፥ "ይህ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ካገኘነው ምርኮ ለእናንተ የተላከ ስጦታ ነው“ብሎ ለይሁዳ ሽማግሌዎችና ለወዳጆቹ ላከላቸው።
27የላከውም፥ በቤቴል፥ በደቡብ ራሞት፥ በየቲር፥
28በአሮኤር፥ በሢፍሞት፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ ሽማግሌዎች ነበር።
29እንዲሁም በራካል፥ በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞች፥
30በሔርማ፥ በቦራሣን፥ በዓታክ፥
31በኬብሮን፥ እንዲሁም ዳዊት ራሱና ሰዎቹ አዘውትረው ይሄዱባቸው በነበሩ ስፍራዎች ሁሉ ለሚኖሩ ሽማግሌዎች ላከላቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።