1ፍልስጥኤማውያንም ሰራዊታቸውን ሁሉ አፌቅ ላይ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ።
2የፍልስጥኤማውያኑ መሳፍንት በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ አለፉ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በደጀንነት አለፉ።
3ከዚያም የፍልስጥኤም መሳፍንት፥ "እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ይሠራሉ?" አሉ። አንኩስም ለሌሎቹ የፍልስጥኤም መሳፍንት፥ "ይህ በእነዚህ ቀናት ሁሉ ከእኔ ጋር የነበረው፥ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ ዳዊት አይደለምን? ደግሞም በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ወደ እኔ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁበትም” አላቸው።
4ነገር ግን የፍልስጥኤም መሳፍንት በእርሱ ላይ ተቆጥተው፥ “ያንን ሰው ወደ ሰጠኸው ወደ ስፍራው እንዲመለስ አሰናብተው፥ በውጊያው ውስጥ ጠላት እንዳይሆንብን ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት አትላከው። ይህ ሰው ከጌታው ጋር ሰላምን የሚፈጥረው በምንድነው? የሰዎቻችንን አንገት በመቁረጥ አይደለምን?
5ይህ በዘፈን እየተቀባበሉ፥ 'ሳኦል ሺዎችን ገደለ፥ ዳዊት ዐሥር ሺዎችን ገደለ" ያሉለት ዳዊት አይደለምን?" አሉት።
6ከዚያም አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ፥ "ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ጥሩ ሰው ነህ፥ በእኔ አመለካከት በሰራዊቱ ውስጥ መውጣትህና መግባትህ መልካም ነው፤ ወደ እኔ ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬው ቀን ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁብህም። ይሁን እንጂ መሳፍንቱ አልደገፉህም።
7ስለዚህ አሁን የፍልስጥኤም መሳፍንት ቅር እንዳይሰኙ ተመለስና በሰላም ሂድ" አለው።
8ዳዊትም አንኩስን፥ “ግን ምን አድርጌአለሁ፥ እንዳልሄድና ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ በእነዚህ በፊትህ በኖርኩባቸው ቀናት በአገልጋይህ ላይ ምን አግኝተህብኛል?” አለው።
9አንኩስም ለዳዊት፥ “አንተ በእኔ ዕይታ ነቀፌታ እንደማይገኝበት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፤ ይሁንና የፍልስጥኤም መሳፍንት፥ 'ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት አይሄድም' ብለዋል።
10ስለዚህ ከአንተ ጋር ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማልዳችሁ ተነሡ፤ ማልዳችሁ ተነሡና ሲነጋላችሁ ሂዱ" ብሎ መለሰለት።
11ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ በጠዋት ለመሄድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ለመመለስ ማልደው ተነሡ። ፍልስጥኤማውያን ግን ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።