1ሐናም እንዲህ በማለት ጸለየች፥ “ልቤ በእግዚአሔር በደስታ ተሞላ። ቀንዴም በእግዚአብሔር ከፍ አለ። በማዳንህ ደስ ብሎኛልና አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ።
2አንተን የሚመስልህ የለምና፥ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለም፤ እንደ አምላካችን ያለም ዐለት የለም።
3ከእንግዲህ አትታበዩ፤ አንዳች የዕብሪት ንግግር ከአፋችሁ አይውጣ። እግዚአብሔር ዐዋቂ አምላክ ነውና፤ ሥራዎች ሁሉ በእርሱ ይመዘናሉ።
4የኃያላን ሰዎች ቀስት ተሰብሯል፥ የተሰናከሉት ግን ኃይልን ታጥቀዋል።
5ጠግበው የነበሩት እንጀራ ለማግኘት ሲሉ ለሥራ ተቀጠሩ፤ ተርበው የነበሩት ረሃብተኝነታቸው አብቅቷል። መካኒቱ እንኳን ሰባት ወልዳለች፥ ብዙ ልጆች የነበሯት ሴት ግን ጠውልጋለች።
6እግዚአብሔር ይገድላል፥ ያድናልም። ወደ ሲዖል ያወርዳል፥ ያነሣልም።
7እግዚአብሔር ድሃ ያደርጋል፥ ባለጸጋም ያደርጋል። እርሱ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ያደርጋል።
8እርሱ ድሃውን ከመሬት ያነሣዋል። ምስኪኖችን ከልዑላን ጋር ሊያስቀምጣቸውና የክብርን ወንበር ሊያወርሳቸው ከአመድ ክምር ላይ ብድግ ያደርጋቸዋል። የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና ዓለምን በእነርሱ ላይ አድርጓል።
9የታመኑ ሰዎችን እግር ይጠብቃል፥ ማንም በኃይሉ አያሸንፍም፤ ክፉዎች ግን በጨለማ ውስጥ ወዳለው ጸጥታ ይጣላሉ።
10እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ይደቅቃሉ፤ እርሱ ከሰማይ ያንጎደጉድባቸዋል። እግዚአብሔር በምድር ዳርቻዎች ላይ ይፈርዳል፤ የእርሱ ለሆነው ንጉሥ ኃይልን ይሰጠዋል፥ ለቀባውም ቀንዱን ከፍ ያደርግለታል።”
11ከዚያም ሕልቃና በራማ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ። ልጁም በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
12የዔሊ ወንዶች ልጆች ምንም የማይረቡ ነበሩ። እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር።
13የካህናቱ ልማድ ከሕዝቡ ጋር እንደዚያ ነበርና፥ ማንኛውም ሰው መሥዋዕት ሲያቀርብ፥ ሥጋው እየተቀቀለ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ይዞ ይመጣ ነበር።
14እርሱም ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ ውስጥ ያጠልቀው ነበር። ሜንጦው ያወጣውንም ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር። ይህንን ወደዚያ ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉ ነበር።
15ይልቁንም ስቡን ከማቃጠላቸው በፊት የካህኑ አገልጋይ ይመጣና የሚሠዋውን ሰው፥ “ጥሬውን ብቻ እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይቀበልምና ለካህኑ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ" ይለው ነበር።
16ሰውየው፥ "መጀመሪያ ስቡን ማቃጠል አለባቸው፥ ከዚያም የፈለከውን ያህል መውሰድ ትችላለህ" ካለው ያ ሰው መልሶ፥ "አይደለም፥ አሁኑኑ ስጠኝ፤ እምቢ ካልክም በግድ እወስደዋለሁ" ይለው ነበር።
17የእግዚአብሔርን መስዋዕት ንቀዋልና የእነዚህ ወጣቶች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበር።
18ትንሹ ልጅ ሳሙኤል ግን ከተልባ እግር ጨርቅ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
19እናቱም ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ ከባሏ ጋር በምትመጣበት ጊዜ በየዓመቱ አነስተኛ መደረቢያ ልብስ እየሠራች ታመጣለት ነበር።
20ዔሊም ሕልቃናን እና ሚስቱን እንዲህ በማለት ባረካቸው፥”ከእግዚአብሔር በለመነችው ልመና ምክንያት እግዚአብሔር ከዚህች ሴት ተጨማሪ ልጆችን ይስጥህ።“ ከዚያም ወደ ራሳቸው መኖሪያ ተመለሱ።
21እግዚአብሔር እንደገና ሐናን ረዳት፥ እንደገናም አረገዘች። እርሷም ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴት ልጆችን ወለደች። እንዲሁም ትንሹ ልጅ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።
22ዔሊ በጣም አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹ በእስራኤላውያን ሁሉ ላይ እያደረጉ ያሉትን በሙሉ እና በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።
23እርሱም እንዲህ አላቸው፥”ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና እንደዚህ ያሉትን ነገሮች የምትፈጽሙት ለምንድነው?
24ልጆቼ ሆይ፥ የምሰማው መልካም ወሬ አይደለምና ልክ አይደላችሁም። የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲያምጽ ታደርጉታላችሁ።
25አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፥ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ይፈርዳል፤ አንድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአትን ቢሠራ ስለ እርሱ የሚናገር ማን ነው?" እነርሱ ግን እግዚአሔር ሊገድላቸው ፈልጓልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም።
26ትንሹም ልጅ ሳሙኤል አደገ፥ በእግዚአብሔርና በሰዎችም ፊት ደግሞ በሞገስ እያደገ ሄደ።
27አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ 'በግብፅ አገር፥ በፈርዖን ቤት ባሪያዎች በነበሩ ጊዜ ለአባትህ ቤት ራሴን ገለጥኩኝ፤
28ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ካህን እንዲሆነኝ፥ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፥ ዕጣን እንዲያጥንልኝ፥ በፊቴም ኤፉድ እንዲለብስ መረጥኩት። የእስራኤል ሕዝብ በእሳት የሚያቀርበውን መባ ሁሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።
29ታዲያ በማደሪያዬ ያዘዝኩትን መሥዋዕትና መባ የምትንቁት ለምንድነው? በሕዝቤ በእስራኤል ከሚቀርበው መስዋዕት ሁሉ በተመረጠው እየወፈራችሁ ልጆችህን ከእኔ በላይ ያከበርከው ለምንድነው?'
30የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ 'ቤትህና የአባትህ ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲመላለስ ተስፋ ሰጥቼ ነበር'። አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ 'ይህንን ማድረግ ከእኔ ይራቅ፥ የሚያከብሩኝን አከብራለሁና የሚንቁኝ ግን ፈጽሞ ይናቃሉ።
31ተመልከት፥ ከእንግዲህ በቤትህ ሽማግሌ የሚሆን አንድም ሰው እንዳይኖር ያንተን ኃይልና የአባትህን ቤት ኃይል የምቆርጥበት ቀን ቀርቧል።
32በማድርበት ስፍራም መከራን ታያለህ። ለእስራኤል መልካም ነገር ቢሰጥም ከእንግዲህ በቤትህ ሽማግሌ የሚሆን አንድ ሰው አይኖርም።
33ያንተ የሆኑትና ከመሠዊያዬ የማልቆርጣቸው ማናቸውም ዐይኖችህን እንዲያፈዝዙና ሕይወትህን በሐዘን እንዲሞሉት አደርጋቸዋለሁ። በቤተ ሰብህ ውስጥ የተወለዱ ወንዶች ሁሉ ይሞታሉ።
34በሁለቱ ወንዶች ልጆችህ በአፍኒን እና በፊንሐስ የሚደርስባቸው ምልክት ይሆንሃል፤ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ።
35በልቤና በነፍሴ ውስጥ ያለውን የሚፈጽም ታማኝ ካህን ለራሴ አስነሣለሁ። የማያጠራጥር ቤት እሠራለታለሁ፤ ለዘላለምም በቀባሁት ንጉሥ ፊት ይሄዳል።
36ከቤተ ሰብህ የተረፈ ሁሉ ጥቂት ጥሬ ብርና ቁራሽ እንጀራ እንዲሰጠው ለመለመን በዚያ ሰው ፊት መጥቶ ይሰግዳል፥ 'ቁራሽ እንጀራ መብላት እንድችል እባክህ ከካህናቱ ኃላፊነቶች በአንዱ ስፍራ መድበኝ'" ይለዋል።