መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 28

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያም ዘመን ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን ሁሉ በአንድ ላይ ሰበሰቡ። አንኩስም ዳዊትን፥ “አንተና ሰዎችህ ያለ ጥርጥር ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ እንደምትወጡ ዕወቅ” አለው።
2ዳዊትም አንኩስን፥ “ስለዚህ አገልጋይህ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ታያለህ” አለው። አንኩስም ዳዊትን፥ “ስለዚህ እኔም በቋሚነት የግል ጠባቂዬ አደርግሃለሁ" አለው።
3ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤል ሁሉ አልቅሰውለት በከተማው በራማም ቀብረውት ነበር። ሳኦል ከሙታንና ከመናፍስት ጋር የሚነጋገሩትን ከምድሪቱ አጥፍቶ ነበር።
4ፍልስጥኤማውያን በአንድነት ተሰባስበው በመምጣት ሱነም ላይ ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን በሙሉ በአንድነት ሰብስቦ ጊልቦዓ ላይ ሰፈረ።
5ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ።
6ይረዳው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜም እግዚአብሔር በህልም፥ ወይም በኡሪም፥ ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።
7ከዚያም ሳኦል አገልጋዮቹን፥ "ወደ እርሷ ሄጄ ምክሯን እንድጠይቅ ከሞተ ጋር መነጋገር እችላለሁ የምትል ሴት ካለች ፈልጉልኝ" አላቸው። አገልጋዮቹም፥ "ከሞተ ጋር መነጋገር እችላለሁ የምትል ሴት በዓይንዶር አለች" አሉት።
8ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ ራሱን ቀይሮ ከሁለት ሰዎች ጋር ሄደ፤ እነርሱም በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄዱ። እርሱም፥ "የምነግርሽን ሰው አስነሥተሽ ከሞተው ጋር በመነጋገር እንድትጠነቁይልኝ እለምንሻለሁ" አላት።
9ሴቲቱም፥ "ሳኦል ከሙታንና ከመናፍስት ጋር የሚነጋገሩትን ከምድሪቱ በማጥፋት ያደረገውን ታውቃለህ። ታዲያ እንድሞት ለሕይወቴ ወጥመድ የምታዘጋጀው ለምንድነው?" አለችው።
10ሳኦልም በእግዚአብሔር ስም ምሎላት፥ "ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ጉዳይ ምንም ቅጣት አይደርስብሽም” አላት።
11ሴቲቱም፥ “ማንን ላስነሣልህ?” አለችው። ሳኦልም፥ “ ሳሙኤልን አስነሽልኝ” አላት።
12ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኻ ሳኦልን፥ "አንተ ራስህ ሳኦል ሆንህ ሳለ ለምን አታለልከኝ?" አለችው።
13ንጉሡም፥ "አትፍሪ፤ ምንድነው ያየሽው?" አላት። ሴቲቱም ሳኦልን፥ "አንድ መንፈስ ከምድር ሲወጣ አያለሁ" አለችው።
14እርሱም፥ “ምን ይመስላል?” አላት። እርሷም፥ "አንድ ካባ የለበሰ ሽማግሌ እየመጣ ነው" አለችው። ሳኦልም ሳሙኤል እንደሆነ ዐወቀ፥ አክብሮቱን ለማሳየትም በምድር ላይ ሰገደለት።
15ሳሙኤልም ሳኦልን፥ "እኔን በማስነሣት የምታስቸግረኝ ለምንድነው?" አለው። ሳኦልም፥ "በጣም ተጨንቄአለሁ፥ ፍልስጥኤማውያን ጦርነት ዐውጀውብኛል፥ እግዚአብሔር ትቶኛል፥ በሕልምም ሆነ በነቢያት አይመልስልኝም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንድታስታውቀኝ ለዚህ ነው የጠራሁህ" ብሎ መለሰለት።
16ሳሙኤልም እንዲህ አለው፥ "ታዲያ እግዚአብሔር ከተወህና ጠላት ከሆነህ የምትጠይቀኝ ምንድነው?
17እግዚአብሔር አደርገዋለሁ ብሎ የነገረህን እርሱን ነው ያደረገብህ። እግዚአብሔር መንግሥትን ከእጅህ ቀዶ ለሌላ ሰው፥ ለዳዊት ሰጥቶታል።
18የእግዚአብሔርን ድምፅ ስላልታዘዝክና ጽኑ ቁጣውን በአማሌቅ ላይ ስላልፈጸምክ ዛሬ ይህንን አድርጎብሃል።
19በተጨማሪም እግዚአብሔር አንተንና እስራኤልን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል። አንተና ልጆችህ ነገ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ። በተጨማሪም እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።“
20ከዚያም ሳኦል በሳሙኤል ቃል ምክንያት እጅግ ስለፈራ ወዲያውኑ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ። በዚያ ቀንና ሌሊት ምግብ ስላልበላ ምንም አቅም አልነበረውም።
21ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጥታ እጅግ መጨነቁን አየች፥ እርሷም እንዲህ አለችው፥ "እኔ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ ሕይወቴን በእጄ ላይ ጥዬ የነገርከኝን ቃል ሰምቻለሁ።
22አሁንም እንግዲህ አንተም ደግሞ የእኔን የአገልጋይህን ቃል እንድትሰማና ጥቂት ምግብ እንዳቀርብልህ እለምንሃለሁ። መንገድህን ለመሄድ ዐቅም እንድታገኝ ብላ።
23ሳኦል ግን፥ "አልበላም" በማለት እንቢ አለ። ነገር ግን አገልጋዮቹ ከሴቲቱ ጋር በመሆን ለመኑት፥ እርሱም ቃላቸውን ሰማ። ስለዚህ ከምድር ላይ ተነሥቶ ዐልጋ ላይ ተቀመጠ።
24ሴቲቱም በቤቷ የደለበ ጥጃ ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰችው፤ ቂጣ አድርጋም ጋገረችው።
25እርሷም በሳኦልና በአገልጋዮቹ ፊት አቀረበችላቸው፥ እነርሱም በሉ። ከዚያም በዚያው ሌሊት ተነሥተው ሄዱ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።