1ዚፋውያን ወደ ሳኦል ወደ ጊብዓ መጥተው፥ “ዳዊት በምድረ በዳው ፊት ለፊት በኤኬላ ኮረብታ ላይ ተደብቋል?” አሉት።
2ከዚያም ሳኦል ተነሣ፥ ከእስራኤል የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ዳዊትን ለመፈለግ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ።
3ሳኦልም በምድረ በዳው ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ፥ በመንገዱ ዳር ሰፈረ። ዳዊት ግን በምድረ በዳው ቆይቶ ነበር፥ ሳኦል በምድረ በዳው ከበስተኋላው እንደመጣ አየ።
4ስለዚህ ዳዊት ሰላዮችን ላከና በርግጥም ሳኦል በመምጣት ላይ መሆኑን ዐወቀ።
5ዳዊት ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ስፍራ ሄደ፤ ሳኦልና የሰራዊቱ አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፥ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር፥ ሁሉም እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር።
6ከዚያም ዳዊት ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የኢዮአብን ወንድም የጽሩያን ልጅ አቢሳን፥ "ወደ ሳኦል ወደ ጦር ሰፈሩ ውስጥ ከእኔ ጋር የሚወርድ ማነው?" አላቸው። አቢሳም፥ "እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ" አለው።
7ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ወደ ሰራዊቱ ሄዱ። ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ፥ ጦሩም ከራስጌው በምድር ላይ ተተክሎ ነበር። አበኔርና ወታደሮቹ በዙሪያው ተኝተው ነበር።
8አቢሳም ዳዊትን፥ "እግዚአብሔር ዛሬ ጠላትህን በእጅህ ላይ ጣለው። አሁንም፥ በአንድ ምት ብቻ በጦር ከምድር ጋር እንዳጣብቀው ፍቀድልኝ፥ ሁለተኛ መምታትም አያስፈልገኝም" አለው።
9ዳዊትም አቢሳን እንዲህ አለው፥ "አትግደለው፤ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን ዘርግቶ ከበደል መንጻት የሚችል ማነው?
10ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይገድለዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ጦርነት ሄዶ ይሞታል።
11እርሱ በቀባው ላይ እጄን ማንሣትን እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁን ግን፥ በራስጌው ያለውን ጦርና የውሃውን ኮዳ ይዘህ እንድንሄድ እለምንሃለሁ።"
12ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ የነበረውን ጦርና የውሃ ኮዳ ወሰደና ሄዱ። ከእግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ስለወደቀባቸው ሁሉም አንቀላፍተው ነበርና አንድም የነቃ፥ ያየ ወይም ያወቀ አልነበረም።
13ከዚያም ዳዊት በሌላኛው ወገን ወጣ፥ በተራራው ጫፍ ላይም ርቆ ቆመ፤ በመካከላቸው ሰፊ ርቀት ነበረ።
14ዳዊትም ወደ ኔር ልጅ ወደ አበኔርና ወደ ሕዝቡ ጮኾ፥ "አበኔር ሆይ፥ አትመልስምን?" አለው። አበኔርም፥ "በንጉሡ ላይ የምትጮኸው አንተ ማነህ?" ብሎ መለሰለት።
15ዳዊትም አበኔርን፥ "አንተ ጀግና አይደለህም? በእስራኤልስ አንተን የሚመስልህ ማነው? ታዲያ ጌታህን ንጉሡን ያልጠበቅኸው ለምንድነው? አንድ ሰው ጌታህን ንጉሡን ለመግደል መጥቶ ነበርና።
16ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም። ሕያው እግዚአብሔርን! ሞት የሚገባህ ነህ፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር የቀባውን ጌታህን አልጠበቅኸውም። አሁንም፥ የንጉሡ ጦርና በራስጌው የነበረው የውሃ ኮዳ የት እንዳለ ተመልከት" አለው።
17ሳኦልም የዳዊት ድምፅ መሆኑን ለየና፥ "ልጄ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነው?" አለው። ዳዊትም፥ "ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ድምፄ ነው" አለው።
18እርሱም እንዲህ አለው፥ "ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ለምንድነው? ምን አድርጌአለሁ? በእጄስ ያለው ክፋት ምንድነው?
19አሁንም ጌታዬ ንጉሡ የአገልጋይህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ። በእኔ ላይ ያነሣሣህ እግዚአብሔር ከሆነ መስዋዕትን ይቀበል፤ ሰዎች ከሆኑ ግን በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፥ 'ሄደህ ሌሎች አማልክቶችን አምልክ' ብለው የእግዚአብሔርን ርስት አጥብቄ እንዳልይዝ ዛሬ አባረውኛልና።
20ስለዚህ፥ አንድ ሰው በተራሮች ላይ ቆቅን እንደሚያድን፥ የእስራኤል ንጉሥ ቁንጫን ለመፈለግ መጥቷልና ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።“
21ከዚያም ሳኦል፥”ኃጢአትን አድርጌአለሁ። ልጄ ዳዊት፥ ተመለስ፤ ዛሬ ሕይወቴ በዐይንህ ፊት ከብራለችና ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ አላደርግብህም። ስንፍናን አድርጌአለሁ፥ እጅግም ተሳስቻለሁ“ አለው።
22ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰለት፥”ንጉሥ ሆይ ተመልከት! ጦርህ ያለው እዚህ ነው፥ ከወጣቶቹ አንዱ ይምጣና ይውሰድልህ።
23ዛሬ እግዚአብሔር በእጄ ላይ ጥሎህ እያለ በእርሱ የተቀባውን አልመታሁትምና እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደ ጽድቁና ታማኝነቱ ይክፈለው።
24ተመልከት፥ ዛሬ ሕይወትህ በዐይኔ ፊት እንደ ከበረች የእኔም ሕይወት በእግዚአብሔር ዐይን አብልጣ የከበረች ትሁን፥ ከመከራዬም ሁሉ ያድነኝ።“
25ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥”ልጄ ዳዊት፥ በርግጥ ታላላቅ ነገሮችን እንድታደርግና እንዲከናወንልህ የተባረክህ ሁን“ አለው። ስለዚህ ዳዊት መንገዱን ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።