1ሳሙኤል ሞተ። እስራኤላውያን ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በራማም በቤቱ ቀበሩት። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
2በማዖን አንድ ሰው ነበር፥ ንብረቱም በቀርሜሎስ ይኖር ነበር። ሰውዬው እጅግ ባለጸጋ ነበር። እርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት። በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር።
3የሰውየው ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበር። ሴቲቱ ብልህና መልኳም የተዋበ ነበረች። ሰውየው ግን አስቸጋሪና በምግባሩ ክፉ ነበር። እርሱም የካሌብ ቤተ ሰብ ተወላጅ ነበር።
4ዳዊት በምድረ በዳ ውስጥ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ።
5ስለዚህ ዳዊት ዐሥር ወጣቶችን ላከ። ዳዊትም ወጣቶቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወደ ቀርሜሎስ ውጡ፥ ወደ ናባልም ሂዱና በስሜ ሰላምታ አቅርቡለት።
6እርሱንም እንዲህ በሉት፥ 'በብልጽግና ኑር፥ ሰላም ላንተ፥ ለቤትህና ያንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን።
7ሸላቾች እንዳሉህ ሰምቻለሁ። እረኞችህ ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ምንም ጉዳት አላደረስንባቸውም፥ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ አንድም አላጡም።
8ወጣቶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል። አሁንም በግብዣህ ቀን መጥተናልና ወጣቶቼ በዓይንህ ፊት ሞገስ ያግኙ። በእጅህ ያለውን ማንኛውንም ነገር ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት እባክህን ስጠው።"
9የዳዊት ወጣቶች በደረሱ ጊዜ፥ በዳዊት ስም ይህንን ሁሉ ለናባል ነገሩትና ምላሹን ጠበቁ።
10ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች፥ "ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማነው? በእነዚህ ቀናት ከጌቶቻቸው የሚኮበልሉ ብዙ አገልጋዮች አሉ።
11ታዲያ እንጀራዬን፥ ውሃዬንና ለሸላቾቼ ያረድኩትን ሥጋ ወስጄ ከየት እንደ መጡ ለማላውቃቸው ሰዎች መስጠት ይኖርብኛል?" ሲል መለሰላቸው።
12ስለዚህ የዳዊት ወጣቶች ዞረው በመመለስ የተባለውን ሁሉ ነገሩት።
13ዳዊትም ሰዎቹን፥ "ሁሉም ሰው ሰይፉን ይታጠቅ" አለ። ስለዚህ ሁሉም ሰይፎቻቸውን ታጠቁ። ዳዊትም ደግሞ ሰይፉን ታጠቀ። አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ዳዊትን ተከተሉት፥ ሁለት መቶዎቹም ከስንቅና ትጥቃቸው ጋር ቆዩ።
14ነገር ግን ከወጣቶቹ አንዱ፥ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ሲል ነገራት፥”ዳዊት ከምድረ በዳ ለጌታችን ሰላምታ ለማቅረብ መልዕክተኞች ላከ፥ ጌታችን ግን ሰደባቸው።
15ሰዎቹ ግን ለእኛ በጣም ጥሩዎች ነበሩ። በመስኩ ላይ እያለን ከእነርሱ ጋር በሄድንበት ጊዜ ሁሉ አንድም አልጎደለብንም፥ እነርሱም አልጎዱንም።
16በጎቹን እየጠበቅን ከእነርሱ ጋር በቆየንበት ጊዜ ሁሉ ቀንና ሌሊት አጥር ሆነውልን ነበር።
17በጌታችንና በቤተሰቡ ሁሉ ላይ ክፉ ታስቦአልና ይህንን ዕወቂ፥ ምን ማድረግ እንዳለብሽም አስቢበት። እርሱ የሚረባ ሰው አይደለምና ማንም ሊያነጋግረው አይችልም“።
18አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት ጠርሙስ የወይን ጠጅ፥ ቀደም ብሎ የተዘጋጀ አምስት በግ፥ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፥ አንድ መቶ የወይን ዘለላና ሁለት መቶ የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች።
19ከእርሷ ጋር የነበሩትንም ወጣቶች፥ "በፊቴ ቅደሙ፥ እኔም እከተላችኋለሁ" አለቻቸው። ለባልዋ ለናባል ግን አልነገረችውም።
20እርሷም በአህያዋ ላይ በመቀመጥ ተራራውን ተከልላ በመውረድ ላይ እያለች ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፥ እርሷም አገኘቻቸው።
21ዳዊትም፥”የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ እንኳን እንዳይጠፋበት፥ ይህ ሰው የነበረውን ሁሉ በምድረ በዳ መጠበቄ በእርግጥም በከንቱ ነበር፥ ስላደረግሁት በጎነት ክፋትን መልሶልኛልና።
22ነገ ጠዋት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳን ባስቀርለት እግዚአብሔር በእኔ በዳዊት ላይ ይህንኑ ያድርግብኝ፥ ደግሞም ይጨምርብኝ" ብሎ ነበር።
23አቢግያ ዳዊትን ባየችው ጊዜ፥ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት አጎንብሳ ወደ ምድር ሰገደች።
24በእግሩ ላይ ወድቃም እንዲህ አለችው፥ "ጌታዬ ሆይ፥ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን። እባክህን አገልጋይህ እንድናገርህ ፍቀድልኝ፥ የአገልጋይህንም ቃል ስማ።
25ጌታዬ ለዚህ ለማይረባው ናባል ትኩረት አይስጥ፥ እርሱ እንደ ስሙ ነው። ስሙ ናባል ነውና ጅልነትም ከእርሱ ጋር ነው። እኔ አገልጋይህ ግን የላካቸውን የጌታዬን ወጣቶች አላየሁም።
26አሁንም ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው እግዚአብሔር ስም፥ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በራስህ እጅ ከመበቀል እግዚአብሔር አግዶሃልና፥ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ ለማድረግ የሚፈልጉ እንደ ናባል ይሁኑ።
27አሁንም አገልጋይህ ወደ ጌታዬ ያመጣሁት ይህ ስጦታ ጌታዬን ለሚከተሉ ወጣቶች ይሰጥ።
28እባክህን የአገልጋይህን መተላለፍ ይቅር በል፥ አንተ ጌታዬ፥ የእግዚአብሔርን ጦርነት በመዋጋት ላይ ስላለህ፥ እግዚአብሔር በርግጥ ለጌታዬ እውነተኛ የሆነን ቤት ይሠራል፥ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም።
29ሰዎች ተነሥተው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድዱህም የጌታዬ ሕይወት በአምላክህ በእግዚአብሔር በሕያዋን አንድነት የታሰረች ትሆናለች፤ እርሱም የጠላቶችህን ሕይወት ከወንጭፍ ኪስ እንደሚወረወር፥ በወንጭፍ ይወረውራል።
30ይህ በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠህን መልካም ነገር ሁሉ ለጌታዬ በፈጸመ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ መሪ ባደረገህ ጊዜ፥
31ይህ ጉዳይ ሐዘን አይሆንብህም፥ ለጌታዬም የልብ ጸጸት አይሆንም፥ ያለ ምክንያት ደም ያፈሰስክ፥ በራስህም እጅ የተበቀልክ አትሆንም። እግዚአብሔር ለጌታዬ ስኬትን ባመጣልህ ጊዜ አገልጋይህን አስበኝ።"
32ዳዊትም አቢግያን፥ "ዛሬ እንድታገኚኝ የላከሽ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን።
33ደም በማፍሰስ ከሚሆን በደልና በራሴ እጅ ስለ ራሴ ከመበቀል ጠብቀሽኛልና ጥበብሽ የተባረከ ነው፥ አንቺም የተባረክሽ ነሽ።
34በእውነት፥ አንቺን ከመጉዳት የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን፥ እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባትመጪ ኖሮ፥ ያለምንም ጥርጥር ነገ ጠዋት ለናባል አንድ ወንድ ሕፃን ልጅ አይቀርለትም ነበር“ አላት።
35ስለዚህ ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀበላት፤ እርሱም፥ "ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ፤ ይኸው ቃልሽን ሰማሁ፥ ተቀበልኩሽም" አላት።
36አቢግያም ተመልሳ ወደ ናባል ሄደች፤ እርሱም የንጉሥ ግብዣን የመሰለ ግብዣ በቤቱ ያደርግ ነበር፤ ናባልም በጣም ሰከሮ፥ ልቡም ደስ ብሎት ነበር። ስለዚህ እስኪነጋ ድረስ ምንም ነገር አልነገረችውም።
37ከነጋ በኋላ፥ የናባል ስካር በበረደ ጊዜ፥ ሚስቱ እነዚህን ነገሮች ነገረችው፤ ልቡ ቀጥ አለ፥ እርሱም እንደ ድንጋይ ሆነ።
38ዐሥር ቀን ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ስለመታው ሞተ።
39ናባል መሞቱን ዳዊት በሰማ ጊዜ፥”የመሰደቤን ምክንያት ከናባል እጅ የተቀበለና አገልጋዩን ከክፉ የጠበቀ ጌታ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን። እርሱም የናባልን ክፉ ሥራ በራሱ ላይ መለሰበት“ አለ። ከዚያም ዳዊት ወደ አቢግያ መልዕክተኛ ልኮ ሚስት አድርጎ ሊወስዳት አናገራት።
40የዳዊት አገልጋዮች ወደ ቀርሜሎስ፥ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ፥ "ሚስቱ እንድትሆኚው ልንወስድሽ ዳዊት ወዳንቺ ልኮናል" አሏት።
41እርሷም ተነሣች፥ በግምባርዋ ወደ ምድር ሰግዳ፥ "ይኸው፥ ሴት አገልጋይህ፥ የጌታዬን አገልጋዮች እግር የማጥብ አገልጋይ ነኝ" አለች።
42አቢግያም ፈጥና ተነሣች፥ ከተከተሏት ከአምስት ሴት አገልጋዮቿ ጋር በአህያ ተቀመጠች፥ የዳዊትን መልዕክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው።
43በተጨማሪም ዳዊት ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ሚስት እንድትሆነው ወሰዳት፥ ሁለቱም ሚስቶቹ ሆኑ።
44ሳኦል የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን፥ በጋሊም ለሚኖረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።