1ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ በተመለሰ ጊዜ፥ "ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ ውስጥ ነው" ተብሎ ተነገረው።
2ከዚያም ሳኦል ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ ወደ ዓይንጋዲ ሄደ።
3እርሱም በመንገዱ በበጎች ማደሪያ አቅራቢያ ወደነበረ ዋሻ መጣ። ሳኦልም ለመጸዳዳት ወደዚያ ገባ። ዳዊትና ሰዎቹ በዋሻው ውስጥ ከኋላ ጥጉጋ ተቀምጠው ነበር።
4የዳዊት ሰዎችም፥ "'ደስ ያሰኘህን እንድታደርግበት ጠላትህን በእጅህ ላይ አሳልፌ እሰጥሃለሁ' ባለህ ጊዜ እግዚአብሔር የተናገረው ስለዚህ ቀን ነው” አሉት። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ በጸጥታ በደረቱ እየተሳበ ወደ ፊት በመሄድ የሳኦልን የካባውን ጫፍ ቆረጠው።
5ከዚህ በኋላ የሳኦልን የካባውን ጫፍ ስለ ቆረጠ ዳዊትን ኅሊናው ወቀሰው።
6እርሱም ሰዎቹን፥ "እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን በማንሣት እንዲህ ያለውን ነገር ማድረግን እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው" አላቸው።
7ስለዚህ ዳዊት የእርሱን ሰዎች በዚህ ቃል ገሰጻቸው፥ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲጥሉበት አልፈቀደላቸውም። ሳኦል ተነሥቶ ከዋሻው ወጣና መንገዱን ቀጠለ።
8ከዚህ በኋላ ዳዊት ተነሥቶ ከዋሻው በመውጣት ሳኦልን፥ "ጌታዬ፥ ንጉሥ ሆይ!" በማለት ተጣራ። ሳኦል ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በተመለከተ ጊዜ፥ ዳዊት በመስገድ አክብሮትን አሳየው።
9ዳዊትም ሳኦልን፥ “ 'ዳዊት ሊጎዳህ ይፈልጋል' የሚሉህን ሰዎች ለምን ትሰማቸዋለህ?
10በዋሻው በነበርን ጊዜ እግዚአብሔር ዛሬ እጄ ላይ ጥሎህ እንደነበረ ዓይኖችህ አይተዋል። አንዳንዶቹ እንድገድልህ ነግረውኝ ነበር፥ እኔ ግን ራራሁልህ። እኔም፥ 'በእግዚአብሔር የተቀባ ስለሆነ፥ በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም' አልኩኝ።
11አባቴ ሆይ ተመልከት፥ በእጄ ላይ ያለውን የካባህን ቁራጭ ተመልከት። የካባህን ጫፍ ቆረጥኩኝ እንጂ አልገደልኩህም፥ በመሆኑም በእጄ ላይ ክፋትና ክህደት እንደሌለ ዕወቅ፤ ምንም እንኳን ሕይወቴን ለማጥፋት ብታሳድደኝም፥ እኔ አልበደልኩህም።
12እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔር ይበቀልልኝ፥ እጄ ግን ባንተ ላይ አትሆንም።
13የጥንቱ ምሳሌ፥ 'ከክፉ ሰው ክፋት ይወጣል' ይላል። እጄ ግን ባንተ ላይ አትሆንም።
14የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተን ውሻ! ቁንጫን!
15እግዚአብሔር ፈራጅ ይሁን፥ በእኔና በአንተ መካከል ይመልከት፥ ይፍረድም፥ ጉዳዬን ተመልክቶም ከእጅህ እንዳመልጥ ይርዳኝ።”
16ዳዊት ይህንን ቃል ለሳኦል ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፥ ሳኦል፥ “ልጄ ዳዊት! ይህ ድምፅህ ነው?” አለው። ሳኦልም ድምፁን አሰምቶ አለቀሰ።
17እርሱም ዳዊትን እንዲህ አለው፥ "በክፋት ስመልስልህ በደግነት መልሰህልኛልና ከእኔ ይልቅ አንተ ጻድቅ ነህ።
18እግዚአብሔር በእጅህ ላይ በጣለኝ ጊዜ አልገደልከኝምና በጎነትን እንዳደረግህልኝ ዛሬ አሳይተሃል።
19አንድ ሰው ጠላቱን ቢያገኘው በሰላም ያሰናብተዋል? ዛሬ ስላደረግህልኝ ነገር እግዚአብሔር ቸርነትን ያድርግልህ።
20አሁንም፥ በእርግጥ ንጉሥ እንደምትሆንና የእስራኤል መንግሥት በእጅህ እንደሚጸና ዐውቃለሁ።
21ከእኔ በኋላ ዘሮቼን እንደማታጠፋና ስሜንም ከአባቴ ቤት እንደማትደመስሰው በእግዚአብሔር ማልልኝ።"
22ስለዚህ ዳዊት ለሳኦል ማለለት። ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ አምባው ወጡ።