1ለዳዊትም፥ "ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን በመውጋት ላይ ናቸው፥ ዐውድማውንም እየዘረፉ ነው“ ብለው ነገሩት።
2ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔር እንዲረዳው ጸለየ፥ እርሱም፥”እነዚህን ፍልስጥኤማውያን ሄጄ ልምታቸው? “ ብሎ ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን፥”ሂድና ፍልስጥኤማውያንን ምታ፥ ቅዒላንም አድን“ አለው።
3የዳዊት ሰዎችም፥”ተመልከት፥ እዚሁ በይሁዳ ሆነን እየፈራን ነው። በፍልስጥኤማውያን ላይ ወደ ቅዒላ ለመውጣትማ ይልቁን እንዴት አስፈሪ አይሆንብንም? “ አሉት።
4ከዚያም ዳዊት እግዚአብሔር እንዲረዳው እንደገና ጸለየ። እግዚአብሔርም፥”ተነሥ፥ ወደ ቅዒላ ውረድ። በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን እሰጥሃለሁ“ ብሎ መለሰለት።
5ዳዊትና ሰዎቹም ሄደው ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጉ። የቀንድ ከብቶቻቸውን ወሰዱ፥ እነርሱንም በታላቅ አገዳደል መቷቸው። ስለዚህ ዳዊት የቅዒላን ነዋሪዎች አዳናቸው።
6የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ቅዒላ ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር።
7ዳዊት ወደ ቅዒላ መሄዱ ለሳኦል ተነገረው። ሳኦልም፥ "በሮችና መቀርቀሪያዎች ወዳሏት ከተማ በመግባቱ በራሱ ላይ ዘግቷልና እግዚአብሔር በእጄ ላይ ጥሎታል" አለ።
8ሳኦልም ወደ ቅዒላ ወርደው ዳዊትንና ሰዎቹን እንዲከቡ ሠራዊቱን ሁሉ ለጦርነት ጠራቸው።
9ዳዊትም ሳኦል ክፉ ሊያደርግበት እንዳቀደ ዐወቀ። እርሱም ካህኑን አብያታርን፥ "ኤፉዱን ወደዚህ አምጣው" አለው።
10ዳዊትም፥ "የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ሳኦል በእኔ ምክንያት ከተማይቱን ለማጥፋት ወደ ቅዒላ ለመምጣት እንደሚፈልግ አገልጋይህ በእርግጥ ሰምቷል።
11አገልጋይህ እንደ ሰማው፥ ሳኦል ወደዚህ ይወርዳል? የቅዒላ ሰዎችስ በእጁ አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እባክህን ለአገልጋይህ እንድትነግረኝ እለምንሃለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “አዎን፥ ወደዚህ ይወርዳል” አለው።
12ዳዊትም፥ “የቅዒላ ሰዎች እኔንና ሰዎቼን በሳኦል እጅ አሳልፈው ይሰጡናልን?” ብሎ ጠየቀው። እግዚአብሔርም፥ “አሳልፈው ይሰጧችኋል" አለ።
13ከዚያም ዳዊትና ወደ ስድስት መቶ የሚደርሱ ሰዎቹ ተነሡ፥ ከቅዒላም ወጥተው ሄዱ፥ ከቦታ ቦታም እየተዘዋወሩ ሄዱ። ዳዊት ከቅዒላ መሸሹ ለሳኦል ተነገረው፥ እርሱም ማሳደዱን አቆመ።
14ዳዊትም በዚፍ ምድረ በዳ ውስጥ ባለው በኮረብታማው አገር፥ በምድረ በዳው ባለ ምሽግ ውስጥ ኖረ። ሳኦል በየቀኑ ይፈልገው ነበር፥ እግዚአብሔር ግን በእጁ ላይ አልጣለውም።
15ዳዊት በዚፍ ምድረ በዳ ሖሬሽ በተባለ ቦታ ነበር፤ ሳኦልም የእርሱን ሕይወት ለማጥፋት እንደ ወጣ አየ።
16ከዚያም የሳኦል ልጅ ዮናታን ተነሥቶ በሖሬሽ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ሄደ፥ በእግዚአብሔር ስም አበረታታው።
17እንዲህም አለው፥ "የአባቴ የሳኦል እጅ አያገኝህምና አትፍራ። አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ምክትልህ እሆናለሁ። አባቴ ሳኦልም ደግሞ ይህንን ያውቃል።"
18እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ዳዊት በሖሬሽ ቆየ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
19ዚፋውያንም በጊብዓ ወዳለው ወደ ሳኦል መጥተው፥ "ዳዊት ከየሴሞን በስተደቡብ በሚገኘው በኤኬላ ኮረብታ ላይ፥ በሖሬሽ ምሽጎች ውስጥ በመካከላችን ተደብቋል፤
20አሁንም ንጉሥ ሆይ! ወደዚህ ውረድ፥ ደስ ባለህ ጊዜ ወደዚህ ውረድ! በንጉሡ እጅ አሳልፎ የመስጠቱ ድርሻ የእኛ ይሆናል” አሉት።
21ሳኦልም፥ “ስለ እኔ ተቆርቁራችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ።
22ሂዱና በይበልጥ እርግጠኛ ሁኑ። የት እንደ ተደበቀና በዚያ ማን እንዳየው መርምሩና ዕወቁ። እጅግ ተንኮለኛ ስለመሆኑ ተነግሮኛል።
23ስለዚህ ልብ በሉ፥ ራሱን የሚደብቅባቸውን ቦታዎች በሙሉ መርምሩ። የተረጋገጠ መረጃ ይዛችሁልኝ ተመለሱ፥ ከዚያ በኋላ እኔም ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ። በምድሪቱ ላይ ካለ፥ በይሁዳ ሺዎች ሁሉ መካከል እፈልገዋለሁ” አላቸው።
24እነርሱም ተነሡ፥ ሳኦልንም ቀድመው ወደ ዚፍ ሄዱ። ዳዊትና ሰዎቹ ከየሴሞን በስተደቡብ በዓረባ በምትገኘው በማዖን ምድረ በዳ ውስጥ ነበሩ።
25ሳኦልና ሰዎቹም እርሱን ሊፈልጉት ሄዱ። ይህም ለዳዊት ተነገረው፥ ስለዚህ ወደ ዐለታማው ኮረብታ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ውስጥ ኖረ። ሳኦል በሰማ ጊዜ ዳዊትን በማዖን ምድረ በዳ አሳደደው።
26ሳኦል በተራራው በአንዱ ወገን ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተራራው በወዲያኛው ወገን ይሄዱ ነበር። ዳዊት ከሳኦል ለማምለጥ ተቻኮለ። ሳኦልና ሰዎቹ ዳዊትንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ለመያዝ እየከበቧቸው በነበሩበት ጊዜ
27አንድ መልዕክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ፥ “ፍልስጥኤማውያን ምድሪቱን ወረዋታልና ፈጥነህ ና" አለው።
28ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን ከማሳደድ ተመልሶ ፍልስጥኤማውያንን ለመዋጋት ሄደ። በዚህ ምክንያት ያ ስፍራ የማምለጫ ዐለት ተብሎ ተጠራ።
29ዳዊት ከዚያ ወጥቶ በዓይንጋዲ ባሉ ምሽጎች ውስጥ ኖረ።