መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለዚህ ዳዊት ያንን ትቶ ወደ ዓዶላም ዋሻ አመለጠ። ወንድሞቹና የአባቱ ቤተሰብ በሙሉ ይህንን በሰሙ ጊዜ ወደዚያ ወደ እርሱ ወረዱ።
2የተጨነቁ፥ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ዳዊትም አዛዣቸው ሆነ። ከእርሱም ጋር ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ።
3ዳዊት ከዚያ በሞዓብ ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ። እርሱም የሞዓብን ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ እባክህን አባቴና እናቴ አንተጋ እንዲኖሩ ፈቃድህ ይሁን” አለው።
4እነርሱንም በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ ተዋቸው። ዳዊት በጠንካራው ምሽግ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ አባቱና እናቱ ከንጉሡ ጋር ኖሩ።
5ከዚያም ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፥ “በጠንካራው ምሽግ ውስጥ አትቆይ። እርሱን ትተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ያንን ትቶ ወደ ሔሬት ጫካ ሄደ።
6ዳዊት ከእርሱ ጋር ከነበሩት ሰዎች ጋር መገኘቱን ሳኦል ሰማ። ሳኦል በጊብዓ ከአጣጥ ዛፍ ስር በእጁ ጦሩን እንደያዘ ተቀምጦ ነበር፥ አገልጋዮቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር።
7ሳኦል በዙሪያው የቆሙትን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የብንያም ሰዎች ሆይ፥ አሁን ስሙ! የእሴይ ልጅ ለእያንዳንዳችሁ እርሻና የወይን ቦታ ይሰጣችኋል? ሁላችሁም በእኔ ላይ ስላደማችሁበት ምትክ ሻለቆችና መቶ አለቆችስ አድርጎ ይሾማችኋል?
8ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ከእናንተ አንዱም አልነገረኝም። አንዳችሁም ስለ እኔ አላዘናችሁም። ልጄ አገልጋዬን ዳዊትን በእኔ ላይ ሲያነሣሣው ከእናንተ ማንም አልነገረኝም። ዛሬ ተደብቋል፥ እኔን ለማጥቃትም ይጠባበቃል።"
9ከዚያም በሳኦል አገልጋዮች መካከል ቆሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ፥ "የእሴይን ልጅ ወደ ኖብ፥ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ መጥቶ አይቼዋለሁ።
10አቤሜሌክም እግዚአብሔር ዳዊትን እንዲረዳው ጸለየለት፥ እርሱም ስንቅና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው" አለው።
11ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክንና የአባቱን ቤተሰብ በሙሉ፥ እንዲሁም በኖብ ይኖሩ የነበሩትን ካህናት እንዲጠራ መልዕክተኛ ላከ። ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ።
12ሳኦልም፥ "የአኪጦብ ልጅ ሆይ፥ አሁን ስማ!" አለው። እርሱም፥ "ጌታዬ ሆይ፥ ይኸው አለሁ” ብሎ መለሰለት።
13ሳኦልም እንዲህ አለው፥ “አንተና የእሴይ ልጅ በእኔ ላይ ያሤራችሁት ለምንድነው? ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ በእኔ ላይ እንዲነሣና በምስጢራዊ ቦታ እንዲደበቅ እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፥ ይረዳው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የጸለይክለት ለምንድነው?”
14አቢሜሌክም ለንጉሡ፥ “የንጉሡ አማችና በጠባቂዎቹ ላይ የበላይ የሆነ፥ በቤትህም የተከበረ፥ በአገልጋዮችህ ሁሉ መካከል እንደ ዳዊት የታመነ ማነው?
15እግዚአብሔር እንዲረዳው ስጸልይለት የዛሬው የመጀመሪያዬ ነውን? ይህ ከእኔ ይራቅ! ንጉሡ ምንም ነገር በአገልጋይህ ወይም በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር። አገልጋይህ ከዚህ ሁሉ ነገር አንዱንም አላውቅምና" ብሎ መለሰለት።
16ንጉሡም፥ "አቢሜሌክ ሆይ፥ አንተና የአባትህ ቤት በሙሉ በእርግጥ ትሞታላችሁ" ብሎ መለሰለት።
17ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን ጠባቂዎች፥ "መሸሹን እያወቁ አላስታወቁኝምና፥ እጃቸውም ከዳዊት ጋር ነውና፥ ዙሩና የእግዚአብሔርን ካህናት ግደሏቸው” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን የእግዚአብሔርን ካህናት ለመግደል እጆቻቸውን አላነሡም።
18ከዚያም ንጉሡ ዶይቅን፥ "ዙርና ካህናቱን ግደላቸው" አለው። ስለዚህ ኤዶማዊው ዶይቅ ዞረና መታቸው፤ በዚያም ቀን ከተልባ እግር የተሠራ ኤፉድ የለበሱ ሰማንያ አምስት ሰዎችን ገደለ።
19እርሱም የካህናቱን ከተማ ኖብን፥ ወንዶችንና ሴቶችን፥ ልጆችንና ሕፃናትን፥ በሬዎችን፥ አህዮችንና በጎችን በሰይፍ ስለት መታቸው። ሁሉንም በሰይፍ ስለት ገደላቸው።
20ነገር ግን አብያታር የተባለው የአኪጦብ ልጅ፥ የአቢሜሌክ ልጅ አመለጠ፥ ወደ ዳዊትም ሸሸ።
21አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ገደለ ለዳዊት ነገረው።
22ዳዊትም አብያታርን፥ “ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያ በነበረ ጊዜ በእርግጥ ለሳኦል እንደሚነግረው በዚያን ቀን ዐውቄ ነበር። ለአባትህ ቤተ ሰብ ሁሉ መሞት ተጠያቂው እኔ ነኝ! ።
23ከእኔ ጋር ተቀመጥ፥ አትፍራ። ያንተን ነፍስ የሚፈልግ የእኔንም ነፍስ የሚፈልግ ነው። ከእኔ ጋር በሰላም ትኖራለህ” አለው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።